የአፍሪካ አገራት የኢትዮጵያን ፖሊሲና እስትራቴጂ በአርዓያነት መጠቀም ጀመሩ

155
አዲስ አበባ ግንቦት 9/2010 ኢትዮጵያ ያስመዘገበችውን ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት ተከትሎ የአፍሪካ አገራት የአገሪቷን ፖሊሲና እስትራቴጂ በአርዓያነት እየተጠቀሙበት መሆኑ ተገለጸ። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ይናገር ደሴ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ኢትዮጵያ ያስመዘገበችውን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በመመልከት ተሞክሮና ልምድ ለመውሰድ በርካታ የአፍሪካ አገራት ተወካዮቻቸውን ወደ አገሪቷ ልከዋል። በተለይም አዲስ የተመረጡት የሴራሊዮን ፕሬዝዳንት ለምርጫ ማኒፌስቶ የሚሆናቸውን ፖሊሲና እስትራቴጂ ከኢትዮጵያ ለመውሰድ ተቀዳሚ ምርጫቸው አድርገው መምጣታቸውን አስታውሰዋል። የህብረተሰቡ የነቃ የፖለቲካ ተሳትፎ፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና የአገርን ግንባታ ከማረጋገጥ አኳያ የኢትዮጵያን ፖሊሲና ስትራቴጂ ተመራጭ ማድረጋቸውና ልምዱንና ትምህርቱን እንዲያካፍሉዋቸው መጠየቃቸውንም ገልጸዋል። በዚህም ፖሊሲው እና ስትራቴጂውን ለአገራቸው ህዝብ በማስተዋወቅ ለምርጫ ማኒፌስቶ እንደሚጠቀሙበት መናገራቸውን ነው ዶክተር ይናገር ያወሱት። አገራቸው የእርስ በእርስ ጦርነት የተካሄደባትና ህብረተሰቡ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ የሚኖር በመሆኑ፤ ከዚህ አስከፊ የድህነት ኑሮ ህዝባቸውን ማውጣት እንደሚሹ፤ ለዚህም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ፈጣንና ተካታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ በመቻሏ ተሞክሮዋን መቅሰም እንደሚፈልጉ መናገራቸውንም ጠቅሰዋል። ፈጣንና ዘላቂ የኢኮኖሚ ምንጭ የሆነውን ፖሊሲና ስትራቴጂ ከማወቅ ባለፈ ፕሮግራሞችና ዕቅዶችን መረዳት እንፈልጋለን በማለታቸው በስፋትና በጥልቀት እንዳካፈሏቸውም ዶክተር ይናገር ገልጸዋል። የአሁኑ የሴራሊዮን ፕሬዝዳንት ጂሊዬስ ማዳ ቢዮ ለፕሬዝዳንትነት ከመወዳደራቸው ከአራት ወራት በፊት ከኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት  ልምድ ለመቅሰም ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸው የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መስራች፣ መዲናና የዲፕሎማቶች መቀመጫ እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድን ሰላምና መረጋጋት በማረጋገጥ በአህጉሪቷ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ በቀዳሚነት እየተጠራች ትገኛለች ብለዋል። በመሆኑም አሳታፊና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ድህነት ቅነሳና አገር ግንባታ ላይ በቅድሚያ ትኩረት ሰጥተን መስራት እንፈልጋለንም ነው ያሉት። ‘’እኛ በጣም ውጤታማ መሆን እንፈልጋለን፤ በመሆኑም ስራችሁን ወደ ተግባር ከመለወጥ አኳያ የተከተላችሁትን ዘዴ መከተል እንሻለን‘’ በማለት ፕሬዝዳንቱ በወቅቱ ፍላጎታቸውን ገልጸዋል። ሌላው የፓርቲው ተወካይ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ያለውን ልምድ በማካፈል በኩል ላደረገልን ትብብር ምስጋናችን የላቀ ነው ሲሉ ይናገራሉ። ባለፈው ሳምንት በተከናወነው  ምርጫም የሴራሊዮን ህዝቦች ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት  53 ዓመቱ ጁሊዬስ ማዳ ቢዩ 51 ነጥብ 8 በመቶ ድምጽ ሲያገኙ የአገሪቷ ገዢ ፓርቲን የወከሉት ሳሙራ ካማራ በበኩላቸው 48 ነጥብ 2 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውን የአገሪቷ ምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል። የአገሪቷ መሪ ሆነው የተመረጡት ጁሊዬስ ማዳ ቢዩም ቃለ መሓላ መፈጸማቸውን የአገሪቷ የፍትህ ሚኒስትር ተጠሪ አብዱላሂ ቻርም አስታውቀዋል፡፡ ቃለ መሐላው በአፋጣኝ እንዲከናወን የተፈለገው በአገሪቷ የስልጣን ክፍተት እንዳይፈጠር ታስቦ መሆኑም ተገልጿል። ናይጀሪያ፣ ማዳጋስካርና ሴራሊዮን የኢትዮጵያን ልምድና ተሞክሮ ለመቅሰም ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ የአፍሪካ ሀገራት መካከል ናቸው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም