"የአየርላንድ መንግስት የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት እንዲጠበቅ እሰራለሁ የሚለውን ሀሳቡን በተግባር ሊያሳይ ይገባል"

122

ጥር 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአየርላንድ መንግስት "የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት እንዲጠበቅ እሰራለሁ" የሚለውን ሀሳቡን በተግባር በማሳየት ከሕዝብና መንግስት ጎን ሊቆም እንደሚገባ ቮይስ ፎር ኢትዮጵያ አየርላንድ ግብረ ሃይል አስታወቀ።

የአየርላንድ መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነቱ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ያልተገባ ጫና ሲያደርግና ለአንድ ወገን ያደላ አቋም ሲያራምድ ቆይቷል።

በተለይም አየርላንድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተደጋጋሚ ጊዜ ስብስባ እንዲጠራ በማድረግ ጫና እንዲፈጠር ግፊት ስታደርግ እንደነበር ይታወቃል።

በአገሪቷ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ይህንን የአየርላንድ አካሄድ በመቃወም የዲፕሎማሲውን ጫና መመከት ላይ የሚሰራ ‘ቮይስ ፎር ኢትዮጵያ አየርላንድ’ የተሰኘ ግብረ ሃይል አቋቁመው መንቀሳቀስ ጀመሩ።

የግብረ ሃይሉ አባል ወይዘሮ ራሔል ዳልተን አየርላንድ በኢትዮጵያ ላይ የምታደረገውን ጫና እንድታቆምና አቋሟን እንድታስተካክልለ የተለያዩ የዲፕሎማሲ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በአየርላንድ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ አባላት የአየርላንድ መንግስትን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባውያን አገራትን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፎች ማካሄዳቸውን ተናግረዋል።

ከሰልፉ ባለፈ ለአየርላንድ ፓርላማ አባላት በተከታታይ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ደብዳቤዎችን በማስገባት እውነታውን እንዲያውቁት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የዳያስፖራ ማህበረሰቡ ሚኒስትሮችን ጨምሮ ከተለያዩ ባለስልጣናት ጋር በመወያየት አየርላንድ በኢትዮጵያ ላይ የምታራምደውን ፖሊሲ እንድታስተካክል ግፊት እያደረጉ መሆኑን አመልክተዋል።

የአየርላንድ ባለስልጣናት የዳያስፖራ ማህበረሰቡ በሚያነጋግራቸው ወቅት የሚሰጡት ምላሽ "የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት እንዲጠበቅ እንሻለን" የሚል መሆኑን የጠቀሱት ወይዘሮ ራሔል ይህን ሀሳባቸውን በተግባር ሊያሳዩ እንደሚገባ በተደጋጋሚ እያስረዳን እንገኛለን ብለዋል።

አየርላንድ ከኢትዮጵያ ሕዝብና በሕጋዊ መንገድ ስልጣን ከያዘው መንግስት ጋር መስራት እንደሚገባትና የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃም የኢትዮጵያን ሕልውና የማስጠበቅ እንደሆነ ሊረዱት እንደሚገባ አስገንዝበናቸዋል ብለዋል።

የአየርላንድ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የያዘው አቋም ሙሉ በሙሉ ባይለወጥም እየተከናወኑ ባሉ የዲፕሎማሲ ጥረቶች በተወሰነ መልኩ በኢትዮጵያ ያለውን እውነታ ወጥቶ የመናገር አዝማሚያዎች በባለስልጣናቱ በኩል እየታዩ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያን መንግስት ብቻ ተጠያቂ የማድረግ ሁኔታ ይታይ እንደነበረና በአሁኑ ሰአት አሸባሪው ሕወሓት የሚፈጽማቸውን አስነዋሪ ድርጊቶች መናገር መጀመራቸውን አመልክተዋል።

የአየርላንድ መገናኛ ብዙሃን የሽብር ቡድኑ የሚፈጽሟችውን ድርጊቶች በዘገባዎቻቸው እያካተቱ እንደሆነ ነው ወይዘሮ ራሔል ያመለከቱት።

ይሁን እንጂ የአየርላንድ መንግስት አሁንም የያዘውን አቋም ማስተካከል እንዳለበትና  የተጀመረውም የዲፕሎማሲ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በአየርላንድ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ጎን መሆናቸውንና የሚፈለገውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም