ሰበር ዜና መንግስት አቶ ስብሃት ነጋ፣ ጃዋር መሐመድና እስክንድር ነጋን ጨምሮ እሥረኞችን ዛሬ በምሕረት ከእሥር ፈታ

805

ታህሳስ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) መንግስት አቶ ስብሃት ነጋ፣ ጃዋር መሐመድና እስክንድር ነጋን ጨምሮ እሥረኞችን ዛሬ በምሕረት ከእሥር መፍታቱ ተገለጸ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ባወጣው መግለጫ “በሕዝብ ይሁንታ የተመረጠ መንግሥት፣ አካታች ሀገራዊ ምክክር እንዲሳካ ከሚጠበቅበት ሞራላዊ ግዴታዎች አንዱ ምሕረት በመሆኑ ለተሻለ ፖለቲካዊ ምኅዳር ሲባል የተወሰኑ እሥረኞችን መንግሥት ዛሬ በምሕረት ከእሥር ፈትቷል” ብሏል።

ምሕረቱ ከዚህ በፊት በተፈጸመ ጥፋት የታሠሩትንም ሆነ በቅርቡ ከተፈጠረው ጦርነት ጋር በተያያዘ የታሠሩትን እንደሚጨምር ጠቁሟል።

“መንግሥት ይሄንን ውሳኔ ሲወስን ዓላማው የኢትዮጵያን ችግሮች ሰላማዊ በሆነ፣ ከእልክና ከመጠፋፋት በራቀ ሁኔታ፣ በሀገራዊ ምክክር በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል መንገድ ለመክፈት ነው” ብሏል።

በተጨማሪም የሕዝብን ጥያቄዎች ከግምት በማስገባትና ምንጊዜም ለሰላማዊ ፖለቲካ መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት እንደሆነ ገልጿል።

በዚህም መሰረት ከእሥር በምሕረት እንዲፈቱ የተወሰነላቸው

1. አቶ ስብሐት ነጋ

2. ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ

3. አቶ ዓባይ ወልዱ

4. አቶ አባዲ ዘሙ

5. ወይዘሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔርና ወይዘሮ ኪሮስ ሐጎስ

6. አቶ ጁሐር መሐመድና በእርሱ መዝገብ የተከሰሱ ሁሉ

7. አቶ እስክንድር ነጋና በእርሱ መዝገብ የተከሰሱ ሁሉ ከእስር መለቀቃቸው ተገልጿል።