ሀገር ስትጣራ አለሁልሽ ማለት ለልጅ የሚነገር ታሪክ ነው- ዳያስፖራዎች

87

አዳማ ታህሳስ 28/2014(ኢዜአ) ሀገር ስትጣራ አለሁልሽ ብሎ መገኘት ለልጅህ የምትነግረው ታሪክ ነው ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት የመጡ ዳያስፖራዎች ገለጹ።

ዳያስፖራዎቹ በቆይታቸው በጦርነት የወደሙ አካባቢዎችን በመጎብኘት ድጋፍ እንደሚያደርጉም ለኢዜአ ተናግረዋል።

"በኢትዮጵያ ላይ እየተሰራጨ ያለውን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በማጋለጥ እውነታውን ለማሳወቅ አበክረን እንሰራለን" ሲሉም ዳያስፖራዎቹ አስታውቀዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባቀረቡት ጥሪ መሠረት ከተለያዩ የውጭ አገሮች ወደ ሀገር ቤት እየመጡ ካሉ መካከል አዳማ ማረፊያቸውን ያደረጉ ዳያስፖራዎች ይገኙበታል።

በአዳማ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ዳያስፖራዎች  መካከል ከእንግሊዝ ለንደን የመጡት አቶ ኢዛና ሙሴ እንደገለጹት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጥሪን በመቀበል የሀገርን ችግር ለመካፈል ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል።

ጥሪውን ሲቀበሉም  አገር በምትፈልጋቸው ቦታ በተግባር ለመገኘት ለራሳቸው ቃል በመግባት ጭምር እንደሆነም ጠቅሰዋል።

"ሀገር ስትጠራህ ደስ ይላል" ያሉት አቶ ኢዛና ሀገር ስትጣራ  አለሁልሽ ብሎ መገኘት ለልጅህ የምትነግረው ታሪክ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

የውስጥና በውጭ ሃይሎች ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ያቀነባበሩትን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በአካል በአገራቸው ተገኝተው  ማጋለጥ ደግሞ ሌላው ወደ ሀገር ቤት የመጡበት አላማ መሆኑንም አመልክተዋል ።

በቆይታቸው አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት የተፈናቀሉ ወገኖችን መርዳትና በጦርነቱ የፈራረሱት የመሠረተ ልማቶችን በመጎብኘት ድጋፍ  ማድረግ ዋና አላማቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

ገንዘባቸውን በሕጋዊ መንገድ በመመንዘር ለኢኮኖሚው እንቅስቃሴ መነቃቃት አስተዋጽኦ እንዳደረጉም ተናግረዋል።

''አገራችን ፈፅሞ ሰላም ናት፤ ሀገሬን ወደ ውጭ ከመውጣቴ በፊት  እንደነበረች ዛሬም አግኝቻታለሁ'' ብለዋል አቶ ኢዛና።

በውጭ ሆነን በኢትዮጵያ መረጋጋትና ሰላም እንደሌለና ወጥቶ መግባት እንደማይቻል ሲያወሩ ለነበሩ አላካት እውነታውን ለማሳወቅ ተግተን እንስራ" ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ከኔዘርላንድ አምስተርዳም ከተማ የመጡት አቶ ዮሐንስ ሰለሞን በበኩላቸው "በኢትዮጵያ ላይ የተሰራጨው የሐሰት ፕሮፓጋንዳ የተለየ አጀንዳ እንዳለው በውጭ የምንኖር ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ማጋለጥ ይገባናል" ብለዋል።

በአገራዊ ጥሪ ወደ ሀገር ቤት የመጡ ዳያስፖራዎች  በኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሰማሩ በመንግሥት በተዘጋጁላቸው  አማራጮች እንዲሳተፉ መልእክት አስተላልፈዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም