በጋና የቁንጅና ውድድር ኢትዮጵያን በመወከልና በማስተዋወቅ የተሳተፈችው ጋናዊት አዲስ አበባ ገባች

ታህሳስ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጋና የኢትዮጵያን ታሪክና ባህል በመወከል እንዲሁም በማስተዋወቅ የተሳተፈችው ዶክተር ሴቶር ኖርግቤ አዲስ አበባ ገባች።

ጋናዊቷ የሜዲካል የአዕምሮ ህክምና ባለሙያና ደራሲ ዶክተር ሴቶር ኖርግቤ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ስልጣኔ፣ ባህላዊ አልባሳት በጋና የቁንጅና መድረክ ላይ በማስተዋወቅ የሀገሯን የቁንጅና ውድድር የመጀመሪያ ዙር ማሸነፏ ይታወቃል።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጥሪ መሰረት በርካታ ዳያስፖራዎች ወደ ሀገር ቤት እየገቡ የሚገኝ ሲሆን በጥሪው መሰረት የኢትዮጵያ ወዳጆችና አፍሪካውያን ጭምር ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ይገኛል።

በሀገሯ ጋና የቁንጅና ውድድር ላይ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ለኢትዮጵያ ያላትን ልዩ ፍቅር የገለጸቸው ጋናዊቷ የሜዲካል የአዕምሮ ህክምና ባለሙያና ደራሲ ዶክተር ሴቶር ኖርግቤ ዛሬ ምሽት አዲስ አበባ ገብታለች።

የኢትዮጵያ ወዳጇ ዶክተር ሴቶር በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ስትደርስም በታዋቂ ሰዎችና የመንግስት የስራ ሃላፊዎች አቀባበል ተደርጎላታል።

''ስለ ኢትዮጵያ ሳናነሳ ስለ አንድነት መነጋገር አይቻልም'' የምትለው ዶክተር ሴቶር ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ስልጣኔ ባለቤት እና የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ ስለመሆኗ ገልጻለች።

ዶክተር ሴቶር ኢትዮጵያን ባስተዋወቀችበት መድረክ የኢትዮጵያን ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና መንፈሳዊ እሴቶች በመድረኩ ላይ በመግለጽ ዳኞችን አስደምማለች።

በድንቅ የመድረክ አቀራረቧም “እኛ አፍሪካውያን አንድ ነን፣ ባህሎቻችን አንድ ህዝብ ያደርጉናል'' ብላለች።

“አሁን የአፍሪካ ህብረት ተብሎ የሚጠራውን የአፍሪካ አንድነት ለማቋቋም ሁለት ታላላቅ ሰዎች ዶክተር ክዋሜ ንክሩማህ እና ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ትልቅ መሰረት ጥለዋል'' ስትል ገልጻ ዶክተር ሴቶር ስለ ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎች፣ የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ፣ የአክሱም ሃውልት እና ጢያ ትክል ድንጋዮችን መዘርዘሯ ይታወሳል።

ኢትዮጵያውያን ልዩ የዘመን አቆጣጠር ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውን የገለጸችው ተወዳዳሪዋ፤ ሀገሪቱ ቅኝ ተገዝታ የማታውቅ ብቸኛዋ አፍሪካዊት አገር ናት ማለቷም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም