የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ የተጎዱ ወገኖችን መልሶ በማቋቋም ሂደት የድርሻውን ይወጣል

ደሴ፣ ታህሳስ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሓት የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም በሚከናወነው ተግባር የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ የድርሻውን እንደሚወጣ አስታወቀ።

አካዳሚው በደሴና በደቡብ ወሎ በአሸባሪው ህወሓት ለተጎዱ ወገኖች ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ እህልና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡

አሸባሪው ህወሓት በደሴ ከተማ ያደረሰውን ውድመት ተዘዋውረው የአካዳሚው ፕሬዚዳንት ዶክተር ደሳለኝ ጴጥሮስ በግለሰቦችና በተቋማት ሀብትና ንብረት ላይ ዘረፋና ውድመት መድረሱ አሳዛኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የወደሙ ተቋማት መልሰው ስራ እንዲጀምሩ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ  የአመራር አካዳሚው የድርሻውን እንደሚወጣ አስታውቀዋል።

ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጠቆሙት ዶክተር ደሳለኝ ''የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ሀገራዊ ግዴታችንን  እንወጣለን'' ብለዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበበ ገብረመስቀል በበኩላቸው የሽብር ቡድኑ በደሴ ከተማ የእምነት ተቋማትን ጭምር ዘርፎና አውድሞ መሸሹን ገልጸዋል፡፡

ተቋማቱን መልሶ በመገንባት ወደ ስራ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባው እስካሁን እየተደረገ ባለው  ርብርብ  በርካታ ተቋማትና የንግድ ማዕከሎች ወደ ስራ መግባታቸውን አስታውቀዋል።

የተቸገሩ ወገኖችን ለመደገፍ እየተደረገ ያለው የእለት ደራሽ እርዳታ ቢቀጥልም ከችግሩ ስፋት አንፃር  ድጋፉ የበለጠ መጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል።

አዲስ አበባ አመራር አካዳሚን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትና የኢትዮጵያ ህዝብ እያደረገ ላለው ሁለተናዊ ድጋፍ ከንቲባው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ በዞኑ ህዝብ ላይ አሰቃቂ ግፍና መከራ ፈጽሟል፤ ንጹሃንን በጀምላ ገድሏል፤ ንብረት ዘርፏል፤ ያልቻለውንም አውድሟል ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተስፋ ዳኜ ናቸው፡፡

በደረሰው ጉዳት ተስፋ ባለመቁረጥ እየተሰሩ ባሉ ስራዎች ጤና ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ወደ ስራ መግባታቸውን አመልክተዋል።

"የተቋማት ስራ መጀመር ህብረተሰቡ ተረጋግቶ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴውን እንዲያከናውን አድርጓል" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም