የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ ለመልሶ ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ ለመልሶ ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ (ኢክናስ) በአሸባሪው ህወሃት የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመገንባት ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታወቀ።
መንግስት ዳያስፖራው በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን የተጎዱ ዜጎችንና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የተጀመረውን ጥረት እንዲደግፍ ጥሪ ማቅረቡ ይታወቃል።
በዚህም የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ ፕሬዝዳንት ዶክተር ትሁት አስፋው የኢክናስ አባላት ኢትዮጵያን ለመደገፍ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ በመገንባት ሂደት እገዛ ከማድረግ በተጨማሪ የመድሐኒትና ሌሎች የሕክምና ግብአቶችን ድጋፍ ለማድረግ ይዘው መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።
የተፈናቀሉ ዜጎችን ያሉበትን ሁኔታ በመመልከት ድጋፍ እንደሚያደርጉና የገና በዓልን ከወገኖቻቸው ጋር አብረው ለማሳለፍ መምጣታቸውንም እንዲሁ።
ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ደም የመለገስ መርሃ ግብር እንደሚካሄድም ነው ዶክተር ትሁት የጠቆሙት።
ጥር 8 ቀን 2014 ዓ.ም ገቢው ለተፈናቀሉት ዜጎች የሚውል የእራት ግብዣ መርሃ ግብር በወዳጅነት አደባባይ እንደሚካሄድም ገልጸዋል።
በእራት ግብዣው ላይ ለመሳተፍ በ"አይዞን ኢትዮጵያ" የኦንላይን የገንዘብ ክፍያ አማራጭ ምዝገባ እየተካሄደ እንደሚገኝና በመተግበሪያው አማካኝነት አንድ ሚሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ እቅድ መያዙን አመልክተዋል።
የእራት ግብዣውን የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ፣ ጌት ፋክትና ሌሎች የዳያስፖራ ተቋማት ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር እንዳዘጋጁት ተናግረዋል።
በካናዳ ኦቶዋ የሚኖሩት የህክምና ባለሙያው ዶክተር ጌትነት አስራት በበኩላቸው በካናዳና አሜሪካ የሚኖሩ የሕክምና ባለሙያዎች ያቋቋሙት 'ሄልዝ ኬር አሊያንስ ፎር ኢትዮጵያ' የተሰኘ ተቋም አባላት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በተለያዩ የህክምና ተቋማት ሙያዊ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተቋሙ የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች በራሳቸው ወጪ የሕክምና መሳሪያዎችን በመግዛት በየወሩ ወደ ኢትዮጵያ ይዞ በመምጣት ድጋፍ ያደርጋሉ፤ሙያዊ አገልግሎት ይሰጣሉ ብለዋል።
እስካሁን በሁለት ዙር የሕክምና መሳሪያዎች ድጋፍ ማድረጋቸውንና የሶስተኛውን ዙር ድጋፍ ወደ ኢትዮጵያ ይዘው መምጣታቸውን አመልክተዋል።
ሌሎች የሕክምና ባለሙያ የሆኑ ዳያስፖራዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲቀላቀሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በመላው ዓለም የሚገኙ ዳያስፖራዎች በሙያቸው ኢትዮጵያን በማገልገል ሀገራቸው የጣለችባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡና የመልሶ ግንባታውን ሂደት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ (ኢክናስ) ከተቋቋመበት ሕዳር ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ለወቅታዊ ሀገራዊ ጥሪና ለልማት ፕሮጀክቶች ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር በላይ በገንዘብና በአይነት በማሰባሰብ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሷል።