በምሁራን የተደረጉ ጥናቶች ወደ ተግባር ለመቀየር ህወሓት አቅጣጫ ማስቀመጡን አስታወቀ

58
መቀሌ ነሀሴ 21/2010 በትግራይ ክልል የልማትና  የመልካም አስተዳደር ግንባታ ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር  በምሁራን የተደረጉ ጥናቶች ወደ ተግባር ለመቀየር ህወሓት አቅጣጫ ማስቀመጡን አስታወቀ። የህወሓት  ማዕከለላዊ ኮሚቴ  ከነሐሴ 18/2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለሶስት ቀናት ባካሄደው ስብሰባ በክልሉና በሃገሪቱ ያሉትን ነባራዊ ሁኔታ መገምገሙን  አመልክቷል፡፡ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ  ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው ምሁራኑ ባለፉት ወራት በክልሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር  ግንባታ ላይ ጥናት ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ጥናቱ የህዝቡን ሁለንተናዊ ፍላጎት ባሟላ መንገድ ተግባራዊ በሚሆንበት አግባብ ማዕከላዊ ኮሚቴው ተወያይቶ አቅጣጫ አስቀምጧል። በኢትዮ ኤርትራ መካከል የተጀመረው ሰላም ዳር እንዲደርስ እንደሚደግፍም ማዕከላዊ ኮሚቴው በመግለጫው አስታውቋል፡፡ ማዕከላዊ ኮሚቴው ሀገራዊ ሁኔታ በገመገመበት ወቅት በህገ መንግስቱና በፌዴራል ስርዓቱ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶችን እንደሚያወግዝም አመልክቷል፡፡ በህወሓት አመራር አባላትና ህዝቡ መካከል የተፈጠረውን አንድነት ለመነጣጠል እየተካሄደ ያለው ዘመቻ ለማምከን እንዲደግፉ ማዕከላዊ ኮሚቴው ለአባላቱና ለህዝቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ማዕከላዊ ኮሚቴው በቀጣይ ለሚያካሂደው ጉባኤ አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመምራትና ወደ  ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር ድርጅቱ ጎልብቶ በሚወጣበት ዙሪያ መወያየቱን ገልፀዋል። " በክልሉ በህጋዊ መንገድ በተደራጀና ባልተደራጀ መንገድ የሚካሄድ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች የዲሞክራሲ ምህዳር ለማስፋትና የህዝባችን ጥቅሞች ለማረጋገጥ ከፍተኛ ትርጉም እንዳላቸው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ይገነዘባል "ብለዋል በመግለጫው። ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በመጠበቅ ፣ የህዝቦችን ክብርና ጥቅም ለማስቀደም ከሚሰሩ ፖለቲካዊ ድርጅቶች   ጋር በጋራ አጀንዳዎች ዙሪያ  አብሮ ለመስራት ህወሓት ዝግጁ መሆኑም ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም