መንግሥት ያልተፈቱ ችግሮችን ለመፍታት በቁርጠኝነት ይሰራል-የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት

52
አዲስ አበባ ግንቦት 9/2010 መንግስት ያልተፈቱ የኅብረተሰብ ችግሮችን ለመፍታት ከምንጊዜውም በላይ በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን የመንግስት ኮሙዬኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ገለጸ። ጽህፈት ቤቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳመለከተው በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተካሄዱ ህዝባዊ ውይይቶች ኅብረተሰቡ በመንግስት በኩል ያሉ ድክመቶችን በማሳየት ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። ባለፉት ጊዜያት እየተደማመሩ የመጡና አዳዲስ ያጋጠሙ ችግሮችን በመፍታት አገሪቷንና ህዝቦቿን ከጥፋትና ውድመት መታደግ ተገቢ እንደሆነም ያወሳል መግለጫው። የኅብረተሰቡን ጥያቄዎችና አገሪቷን ያጋጠሟትን ችግሮች ለመፍታት የተደራጀ ተቋማዊ አፈጻጸም መተግበር አስፈላጊ በመሆኑም ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን፣ አንድነትን፣ የዴሞክራሲ ሥርዓትና የመልካም አስተዳደር ግንባታን ማስቀጠል እንደሚችልም መግለጫው ያትታል። በመሆኑም፣ ህዝቡ የተጀመረውን አገራዊ ሪፎርም ከዳር ለማድረስ በተለመደው አርቆ አሳቢነት፣ ትዕግስትና ጽናት ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ መተኪያ የሌለው ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል መንግሥት ጥሪ አቅርቧል። የመግለጫው ሙሉ ሐሳብ እንደሚከተለው ቀርቧል፡- ጠንካራ ተቋማዊ አሠራር- ለውጤታማ የለውጥ ሥራ! የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲዊ ሪፐብሊክ መንግስት የህዝብን ጥያቄዎች እና ሳይፈቱ እየተንከባለሉ ዛሬ ላይ የደረሱ ችግሮችን ለመፍታት ከምንጊዜውም በላይ በቁርጠኝነት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ መንግሥትን የሚመራው ድርጅት /ኢህአዴግ/ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከታህሳስ 3 ቀን ጀምሮ ለ17 ቀናት ባካሄደው ኮንፈረንስ፣ በአገራችን የሚታዩ የቆዩና ወቅታዊ ችግሮችን በመለየት በመንስኤና መፍትሄዎቻቸው ላይ ከመከረ በኋላ ችግሮቹ የሚፈቱበትን አቅጣጫ አስቀምጦ እንደነበር ይታወሳል። በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች በተካሄዱ ህዝባዊ መድረኮች፣ ህዝባችን በመንግሥት ዘንድ የሚታዩ ጉልህ ድክመቶችን በማሳየት ረገድ መተኪያ የሌለው ሚና ተጫውቷል። መንግስትም ከህዝቡ የተነሱትን ችግሮች በመቀበል እና ለመፍትሄዎቹም በመትጋት በርካታ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ እየተከማመሩ የመጡና አዳዲስ ያጋጠሙ ችግሮችን መፍታት፣ አገራችንን እና ህዝቦቻችንን ከጥፋትና ውድመት የመታደግ ጉዳይ መሆኑ ታምኖበት፣ እንደየችግሮቹ ባህርያት የተቀመጡ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የለውጥ ሥራውን በባለቤትነት የሚመሩ 12 ያህል ግብረ ሃይሎችን በማቋቋም ወደሥራ ተገብቶ ነበር። እነዚህ ግብረሀይሎች በትክክል እና በቀጥታ በህዝቡ ውስጥ ያሉትን በርካታ ጥያቄዎች እና ቅራኔዎች በተገቢው መንገድ መምራት እንዲችሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል ከማድረግ ጀምሮ የለውጡን ሂደት በሚፈለገው ፍጥነት እና መጠን መምራታቸውን በቅርበት ብቻ ሳይሆን በትጋትም ጭምር ለመከታተል ብርቱ ጥረት ተደርጓል፡፡ መንግሥት፣ በቅርቡ የግብረ ሃይሎቹን አፈጻጸም ከገመገመ በኋላ የህዝቡን ጥያቄዎች በአጥጋቢ ሁኔታ ለመፍታትና አገራችን ያጋጠሟትን ችግሮች ውጤታማ በሆነ መንገድ መፍታት የሚቻለው፣ በተደራጀ ተቋማዊ አፈጻጸም መሆኑን ድምዳሜ ላይ ተደርሷል። በመሆኑም ግብረሀይሎቹ እስካሁን ሲያከናውኗቸው የነበሩትን ሥራዎች፣ በቀጥታ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ተቋማት እንዲያስረክቡ በመንግሥት ተወስኗል። በዚህም መሰረት በግብረሀይሉም ሆነ በሚመለከታቸው ተቋመት በኩል ለጉዳዩ ተግባራዊነት ምንም የሚባክን ጊዜ እንደሌለ ታሳቢ ተደርጎ በአፋጣኝ ወደ ትግበራ እንዲገባ ግልጽ እና ጠንካራ አቅጣጫ ተቀምጥዋል፡፡ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ እያካሄደው ያለው የለውጥ ሥራ መነሻውና መድረሻው ህዝብን እያዳመጡ እና እያሳተፉ የአገራችንን ችግሮች መፍታት፣ ጥያቄዎቹን መመለስ፣ ስኬት የተመዘገቡባቸውን የሰላም፣ የልማት እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በማጠናከር የህዝባችንን የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው። ከህዝባችን ጋር ሆነን የማንፈታው አንዳችም ችግር ከቶውንም ሊኖር እንደማይችል በጽኑ የሚገነዘበው የኢፌዴሪ መንግሥት፣ የጋራ ልማትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን፣ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት እና የመልካም አስተዳደር ግንባታን ለማስቀጠል፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት አሠራርን ለማስፈን  እንዲሁም የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በመንግሥት የተጀመረው የለውጥ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መንግሥት በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ ይወዳል። የሪፎርም ሥራው የደረሰበትን ሂደት አስመልክቶም በየጊዜው ለህዝብ የሚያሳውቅ መሆኑን ይገልጻል። በአገራችን የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ዓላማ፣ ህዝብን እያዳመጠ ውጤታማ ምላሽ የሚሰጥ፣ ሲያጠፋ የሚጠየቅ፣ ህዝብን በቅንነት ማገልገል የሚችል ጠንካራ መንግሥታዊ አሠራር መፍጠር ነው። በመሆኑም ሪፎርሙ የአንድ ጀምበር ሥራ ብቻ እንዳልሆነ መገንዘብ ያሻል፤ ህዝባችንም በዚሁ አግባብ መንግስትን እንደሚረዳ እና ለተጀመረው ሁሉን አቀፍ የለውጥ ሂደትም እንደተለመደው የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት መንግስት ያምናል፡፡ ይህ የለውጥ ሂደት ህዝቡ በሚፈልገው ልክ በአጠረ ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ይሆን ዘንድ መላው ህዝባችን ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ መረባረብን ይጠይቃል። በመሆኑም፣ ህዝባችን የተጀመረውን አገራዊ ሪፎርም ከዳር ለማድረስ በተለመደው አርቆ አሳቢነት፣ ትዕግስትና ጽናት ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ መተኪያ የሌለው ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም