የወደሙ ትምህርት ቤቶችን በተሻለ መልኩ መልሶ መገንባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደረገ

59

ታህሳስ 27/2014/ኢዜአ/ የትምህርት ሚኒስቴር በአሸባሪው ህወሃት ውድመት የተፈፀመባቸውን ትምህርት ቤቶች በተሻለ መልኩ መልሶ መገንባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አካሄደ።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ አሸባሪው ቡድን ከፍተኛ ውድመት ከፈፀመባቸው መሰረተ ልማቶች መካከል የትምህርት ተቋማት አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

በትምህርት ቤቶቹ ላይ የደረሰው የውድመት መጠንም 90 በመቶ የሚሆነው ሙሉ ለሙሉ የወደሙና ምንም አይነት አገልግሎት መስጠት የማይችሉበት ደረጃ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

በ27 ዓመታት የትምህርት ተቋማት ግንባታ ቢከናወንም ከቁጥር የዘለለና የሚጨበጥ ስራ አለመከናወኑን ጠቅሰው በተለይም የጥራትና የትውልድ ቀረፃ ጉዳይ ትኩረት ተነፍጎት ቆይቷል ብለዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በተለይም በአፋርና አማራ ክልሎች በወረራ በቆየባቸው ጊዜያት በትምህርት ተቋማት ላይ ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት ፈፅሟል ነው ያሉት።

በመሆኑም ውድመት የተፈፀመባቸውን ትምህርት ቤቶች በተሻለ መልኩ መልሶ መገንባት እንደሚገባ ጠቅሰው የዲዛይን ስራቸው ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት ዶክተር ምህረት ደበበ "የማን ቤት ነው የሚሰራው'' በሚል ርእስ የትምህርት ተቋማት ምን መምሰል እንዳለባቸው የሚዳስስ ጽሁፍ አቅርበዋል።

የትምህርት ቤቶቹ ዘረፋና ውድመት በአገርና ህዝብ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ያስከተለ ቢሆንም ችግሩን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ለተሻለ ግንባታ እድሉን መጠቀም ይገባል ብለዋል።

የትምህርት ቤቶቹ መልሶ ግንባታ ለመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲሁም ለተማሪዎች ምቹና ማራኪ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በዘርፉ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ ካሉ ግለሰቦች መካከል የሚጠቀሰው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ፤ የትምህርት ቤቶች ግንባታ በተለይም በአካባቢው ተፈጥሯዊ ሃብትና ግብዓት ላይ የተመረኮዘ መሆን አለበት ብሏል።  

ኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር ፕሬዝዳንት አማኑኤል ተሾመ፤ የወደሙ ትምህርት ቤቶች መልሶ ግንባታ ራእይ የሚሰነቅበትና የአገር ፍቅር ስሜት የሚታተምበት ጭምር በመሆኑ ትኩረት ያሻዋል ብለዋል።

መልሶ ግንባታው በአብዛኛው ትምህርት ቤቶች ላይ የሚስተዋሉ የመሰረተ ልማት አለመሟላት ችግሮችን በመፍታት በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ የሚያሳድረውን ችግር የሚፈታ መሆን አለበት ነው ያሉት።

የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ ዲዛይን እንደ የአካባቢው መልክአ ምድር፣ የማህበረሰቡ የአኗኗር ዘይቤ እና እሴቶቻቸውን ያካተተ መሆን አለበት ብለዋል።

አሸባሪው ህወሃት በወረራ በቆየባቸው በአማራና አፋር ክልሎች 1 ሺህ 90 ትምህርት ቤቶችን ሙሉ ለሙሉ ማውደሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም