በሀገር ላይ የተጋረጠውን አደጋ በመቀልበስ የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን እናደርጋለን

56

ታህሳስ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) መንግሥት በሀገር ላይ የተጋረጠውን አደጋ በመቀልበስ የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየሠራ መሆኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ለተጎዱ እና ለመከላከያ ሠራዊት በተግባር እየታየ ያለው የወገን አለኝታነት የሚያኮራ መሆኑን አሳውቀዋል።

ይህ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጥሪ አርቅርበዋል።

ዳያስፖራውም ለሀገራዊ ጥሪው የሰጠው ምላሽ አኩሪ መሆኑን ገልጸው ምስጋና አቅርበዋል።

መንግሥት የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸውን ይገነዘባል ያሉት ሚኒስትሩ፣ ችግሮችን ለማስተካከልም የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጥምር የፀጥታ ኃይሉ ወደ ትግራይ ክልል አንዳይገባ መወሰኑን ተከትሎ መከላከያ ሠራዊት የያዛቸውን ቦታዎች ይዞ እና አፅንቶ እንዲቆይ ተደርጓል፤ ከውሳኔው በኋላ ምንም እንቅስቃሴ አልተደረገም ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት የትግራይ ክልል ሕዝብ ያሉበት ችግሮች እንዲፈቱለት መንግሥት ዝግጁ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣የትግራይ ሕዝብ ለጥቂት የሥልጣን ጥመኞች ሲባል ልጆቹ እንዳይማገዱ አሸባሪውን ህወሓት መቃወም እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።

የትግራይ ክልል ሕዝብ ወደ ቀድሞ ህይወቱ እንዲመለስ ሕዝቡም ሆነ በውጭ የሚኖሩ አካላት በአሸባሪው ህወሓት የደረሰውን ጉዳት መመከት አለበት ብለዋል።

ለዚህም መተባበር እና ሁሉም የበኩሉን አበርክቶ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አሳውቀዋል።

ከአሸባሪው ህወሓት ነፃ በወጡ የአፋር እና የአማራ ክልል አከባቢዎች የተጎዱ ሰዎችን ለመደገፍ እና የወደሙ ተቋማትን መልሶ በመገንባት ወደ መደበኛ ሥራ የመመለስ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአማራም ሆነ በአፋር ክልሎች የዞን አደረጃጀት እና የወረዳ አስተዳደር ወደ ሥራ ገብተዋል፤ የቀበሌ አስተዳደር መዋቅርን ወደ ሥራ ለማስገባት ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ ናቸው ብለዋል።

ነፃ በወጡ አካባቢዎች የቴሌኮም፣ የመብራት እና የባንክ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶችን የማስጀመር ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ላሊበላ እና ወደ ኮምቦልቻ የበረራ ሥራ መጀመሩንም አውስተዋል።

የወደሙ የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች ተቋማትን የመጠገን ሥራ እየተሠራ መሆኑን እና በዚህም ጥገናቸው አልቆ ሥራ የጀመሩ ተቋማት መኖራቸውን መግለጻቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

ቀሪዎቹን ወደ ሥራ ለማስገባት ሁሉም የተጠናከረ ሥራ በመሥራት ላይ ናቸው ብለዋል።

ትርፍ አምራች አካባቢዎች ለተጎዱ አካባቢዎች ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም