ዳያስፖራው በአሸባሪው ህወሃት የወደሙ ከ4 ሺህ 500 በላይ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት ሚናውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

205

ታህሳስ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዳያስፖራው በአሸባሪው ህወሃት የወደሙ ከ4 ሺህ 500 በላይ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት ሚናውን እንዲወጣ ትምህርት ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።

ሚኒስቴሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ሀገር ያለ ትምህርት መቆም እንደማትችል ጠቅሶ፥ ትውልዱ የሚቀረፅባቸው የትምህርት ተቋማት በአሸባሪው ህወሃት መውደማቸውን አስታውሷል።

በአማራና በአፋር ክልሎች በሽብር ቡድኑ ጥቃት 703 ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን ገልጿል።

ሚኒስቴሩ አክሎም 3 ሺህ 887 ትምህርት ቤቶች በከፊል ጉዳት እንደደረሰባቸውና ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንደሆኑ ጠቅሷል።

የወደሙ ትምህርት ቤቶችን ከቀድሞው በተሻለ ለተማሪዎች ምቹ ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ሚኒስቴሩ አመልክቷል።

ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰውን ጫና በመቃወም ያደረገውን ከፍተኛ አስተዋፅኦ በትምህርት መስኩም እንደሚደግመው ፅኑ እምነት አለን ያለው የሚኒስቴሩ መግለጫ፤ ዳያስፖራው የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቋል።

በመማሪያ ክፍሎች ግንባታ፣ በማስተማሪያ ቁሳቁስ አቅርቦት፣ በቤተ-ሙከራ መሳሪያዎች ድጋፍ እና በመሳሰሉ እንቅስቃሴዎች ዳያስፖራው የበኩሉን እንዲወጣ ሚኒስቴሩ ጥሪ አቅርቧል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼