ምክር ቤቱ የመንግስት መስሪያ ቤት ህንጻ ግንባታዎች በተቀመጠላቸው እቅድ እንዲጠናቀቁ ተገቢው ክትትል እንዲደረግ አሳሰበ

210

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) የተጀመሩ የመንግስት መስሪያ ቤት ህንጻ ግንባታዎች በተቀመጠላቸው እቅድ እንዲጠናቀቁ ተገቢው ክትትል እንዲደረግ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ፡፡

በምክር ቤቱ የከተማ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በመዲናዋ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወኑ የሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ህንጻ ግንባታ አፈጻጸም ደረጃን ተመልክቷል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ በዚህን ወቅት የመንግስት መስሪያ ቤቶች ህንጻ ግንባታ አፈጻጸም ከፍተኛ መጓተት እንደሚታይበት ጠቅሰው፤ ይህም የህዝብ ሃብት እንዲባክን እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የህንጻ ግንባታዎች መጓተትም መንግስትን ለአላስፈላጊ የኪራይ ወጪ እንደዳረገው ነው ያነሱት፡፡

በመሆኑም የተጀመሩ የመንግስት መስሪያ ቤት ህንጻ ግንባታዎች በተቀመጠላቸው እቅድ እንዲጠናቀቁ ተገቢው ክትትል እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡

ተቋራጮች በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ኋላ የቀሩ ስራዎችን የማካካስ ስራ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ተቋራጮች በበኩላቸው የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የዋጋ ንረት በግንባታ ስራዎች አፈጻጸም ላይ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የግዥ ሒደት መጓተትና የዲዛይን ስራ ተሟልቶ አለመቅረብም ሌላኛው ምክንያት መሆኑን ነው ያነሱት፡፡

የፌዴራል መንግስት ህንጻዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተክለጻዲቅ ተክለአረጋይ በተቋራጮች በኩል የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተቋራጮች በኩል የሚታዩ ድክመቶችን በማረም ረገድ ውል ከማቋረጥ ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

የክትትልና ቁጥጥር ስራው በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በዛሬው እለት የንግድ ሚኒስቴር፣ ብሔራዊ ቴአትር፣ የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ኤጀንሲ እና የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ህንጻዎችን የግንባታ አፈጻጸም ጎብኝቷል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼