የአብርሆት ቤተ-መፃህፍት ትውልድን በዕውቀት በመገንባት የኢትዮጵያን ቀጣይ የብልጽግና ጉዞ በማፋጠን አስተዋጽኦው የጎላ ነው

141

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአብርሆት ቤተ-መፃህፍት ትውልድን በዕውቀት በመገንባት የኢትዮጵያን ቀጣይ የብልጽግና ጉዞ በማፋጠን የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ።

የአብርሆት ቤተ-መፃህፍት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዛሬው እለት በይፋ ተመርቆ ተከፍቷል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር ፕሮጀክቶችን ማስጀመር ብቻ ሳይሆን መጨረስ እንደሚቻል የዚህ ቤተ-መፃህፍት ምረቃ አመላካች ነው ብለዋል።

በሌሎች ሀገራት አይተን የምንቀናበትን ነገር በኢትዮጵያ መስራት እንደሚቻል የሚያሳይ ቤተ-መፃህፍት መሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን እና ልኳን የሚመጥነው ይሄ ነው ብለዋል።

የቤተ-መፃህፍቱ ስያሜ "አብርሆት" ትርጓሜው እውነትንና ዕውቀትን መሠረት በማድረግ ከድንቁርና ቀንበር ነጻ የመውጣት ሂደት መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ትልቁ ችግር የሆነው "ድንቁርና"  መሆኑን ገልፀው በድንቁርና ምክንያት እርስ በእርስ መባላት፣ የገዛ ሀገሩን ባንዳና ተላላኪ ሆኖ የሚያጠቃ ስለመኖሩ ጠቁመዋል።

ዕውቀት ከድንቁርና ነፃ የሚያወጣ እና የማድረግ እቅም የሚያገለብት፣ ታሪክን፣ ሀገርን ህዝብን ማንነትን የሚያሳውቅ ከጨለማ ወደ ብርሃን የሚያወጣ በመሆኑ ቤተ-መፃህፍቱ በዚህ ረገድ የሚኖረው አስተዋፆ ትልቅ መሆኑን ነው ያነሱት።

የአብርሆት ቤተ-መፃህፍት ትውልድን በዕውቀት በመገንባት የኢትዮጵያን ቀጣይ የብልጽግና ጉዘ በማፋጠን የጎላ አስተዋፆ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

በዓለም ላይ ካሉ 190 ሀገራት 18 ሀገራት ብቻ የራሳቸው ፊደል ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ከእነዚህ ሀገራት አንዷ እና በአፍሪካ አህጉር ብቸኛዋ ስለመሆኗ ተናግረዋል።

ይህንን ለትውልድ ለማሸጋገር ታሪካችንን እና ልካችንን በማወቅ ጠላቶች ኢትዮጵያን መድፈር እንዳያስቡ ማድረግ አለብን ብለዋል።

ቤተ-መፃህፍቱ የትም ዓለም ካለ ቤተ-መፃህፍት ጋር የተስተካከለ መሆኑን ጠቅሰው ሁሉም ቤተመጽሐፍቱን በመጠበቅና በመንከባከብ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው መንግስት አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ አደርጋታለሁ ብሎ ለህዝቡ የገባዉን ቃል በተግባር መፈጸሙን ያረጋገጠበት ነው ብለዋል።

በጦርነት ውስጥ ልማታችንን ሳንገታ ኢትዮጵያን አሸናፊ አድርገናታል ያሉት ከንቲባዋ ቤተ-መፃህፍቱ ለድንቁርና መፈወሻ መድሃኒት የሆነ ሰው ተኮር ልማት ነው ብለዋል። 

በመስዋትነት ወድቀው ዛሬ ቀና እንድንል ያደረጉ እና ኢትዮጵያን ከመፍረስ ላዳኑ የመከላከያ ሰራዊት እና የጸጥታ አካላት ዘላለማዊ ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም