በድህረ ጦርነት የተግባር አንድነት በማንገብ ለህዝብ ተጠቃሚነት እንተጋለን -የደቡብ ከፍተኛ አመራሮች

217

ሀዋሳ፤ ታህሳስ 23/2014 (ኢዜአ ከህልውና ጦርነቱ በኋላ የተግባር አንድነት በማንገብ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ተዘጋጅተናል ሲሉ የደቡብ ክልል ከፍተኛ አመራሮች አስታወቁ።

“ከህልውና ትግላችን ወደ ብልፅግና ጉዟችን” በሚል መሪ ሀሳብ  የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሀዋሳ ከተማ እየተወያዩ ነው።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ጌትነት በጋሻው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ከህልውና ጦርነት በኋላ አመራሩ ህዝቡን በማስተባበር  በሙሉ አቅሙ ፊቱን ወደ ልማት ስራዎች ሊያዞር ይገባል።

“በዚህ ረገድ አመራሩ በቂ ግንዛቤ አግኝቶ እንዲቀሳቀስ የውይይት መድረኩ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው መድረኩ የጋራ አስተሳሰብና የተግበር አንድነት በመፍጠር  ለመረባረብ አዘጓጅቶናል” ብለዋል።

“የውሰጥና የውጭ ሀይሎች በመናበብ በሀገር ላይ የከፈቱትን ጦርነት አመራሩና ህዝቡ እንደ አንድ በመሆን ለመመከት ያደረጉት ጥረት ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ጌትነት “የዞኑ ህዝብም የህልውና ዘመቻውን ለማጠናከር ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ በማድረግ ደጀንነቱን አስመስክሯል” ።

የተገኘውን ድል በአግባቡ ማስተዳደር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው “በቀጣይም በጋራ አጀንዳዎቻችን ላይ ከህዝባችን ጋር በመምከር ለሁለንተናዊ ልማትና ብልጽግና ለመትጋት ተዘጋጅተናል”ሲሉ አስታውቀዋል።

የአማሮ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወገኔ ብዙነህ በበኩላቸው “በህልውና ዘመቻው የተፈጠረውን የህዝብ አንድነትና መነሳሳት ወደ ልማትና መልካም አስተዳደር አጀንዳዎች በመለወጥ ልንጠቀምበት ይገባል” ብለዋል።

ከዚህ አኳያ አመራሩ ወጥ የሆነ ቁመናና የጋራ ተልእኮ በማንገብ ለልማት ስራዎች ተፈጻሚነት የተጣለበትን ተልእኮ  እንዲወጣ በመድርኩ የጋራ መግባባት መፈጠሩን  አመልክተዋል።

“በየአካባቢያችን የሚጠብቁን በርካታ ተልዕኮዎች አሉብን” ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ከጦርነቱ በኋላ የተገኘውን ሰላም ተንተርሰን ወደ ታች በመውረድ ህዝቡን አስተባብረን የተሻለ ስራ ለመስራት ተዘጋጅተናል ” ብለዋል።

የተጀመረውን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በማጠናከርና የህዝቡን የልማት ጥያቄዎችንና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች በተቀናጀ መንገድ ለመፍታት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

“ተገደን የገባንበትን ጦርነት በህብረ ብሔራዊ አንድነት ዘመቻ በመቀልበስ ኢትዮጵያ አሸናፊ የሆነችበትን ድል ተጎናጽፈናል” ያሉት ደግሞ የከምባታ ጠንባሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መለሰ አቲሳ ናቸው።

ዘመቻውን በተባበረ ክንድ እንደመከትነው ሁሉ አሸባሪው በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የደረሰው ውድመትና ኢኮኖሚያዊ ድቀት እንዲያገግም የዞኑን ህዝብ በማስተባበር የሚቻለውን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን  አስታውቀዋል።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዮት ደምሴ በውይይት መድረኩ በህልውና ዘመቻው የተመዘገቡ ድሎችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና  በድህረ ጦርነት ተግባራት ዙሪያ በዝርዝር ውይይት መደረጉን አመልክተዋል።

አመራሩ በድህረ ጦርነት ወቅት በላቀ ትጋትና መነሳሳት የጋራ አላማና ግብ በመያዝ በጊዜ የለንም መንፈስ ለመስራት የጋራ መግባባት ላይ መድረሱን አስታውቀዋል።

በህብረ ብሔራዊ አንድነት ዘመቻ ወቅት የዞኑ አስተዳደርና ህዝብ በሁሉም መስክ የላቃ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ጠቅሰው “በጦርነቱ በአማራና አፋር ህዝብ ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመቋቋም ህዝባችንን አስተባብረን  አበክረን እንሰራለን” ብለዋል።

“ኢትዮጵያን የማፍረስ አጀንዳ ያላቸውን የውስጥና የውጭ ኃይሎች ሴራ እየመከትን የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ማስቀጠል ቀዳሚ አጀንዳችን ነው” ሲሉ ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል።