ተመራቂዎች ለውጤት የሚያበቃና ለውጥን የሚያረጋግጥ ስራ ፈጣራ መሆን ይጠበቅባቸዋል

145

ሐረር ፤ ታህሳስ 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) ተመራቂዎች ከጠባቂነት በመውጣት ለውጤት የሚያበቃና ለውጥን የሚያረጋግጥ ስራ ፈጠራ መሆን እንደሚጠበቅባቸው የሐረሪ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አሳሰቡ።

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ  411 የጤና ባለሙያዎችን ዛሬ ባስመረቀበት ወቅት  በክብር እንግድነት የተገኙት ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፤ አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት ታግዞ ሀገር ለማተራመስ የጠነሰሰው  ሴራ በህዝቦች የተባበረ ክንድ ማክሸፍ ተችሏል።

ተመራቂዎቹም ከድሉ ማግስት በመመረቃቸው ድርብ ድል አግኝታችኋል ብለዋል።

ከጠባቂነት በመውጣት ለውጤት የሚያበቃና  ለውጥን የሚያረጋግጥ ስራ ፈጠራ ለመሆን  ጽናትና ጥንካሬ የታከለበት ተግባር ከተመራቂዎቹ እንደሚጠበቅ ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያሳሰቡት።

ከዚህም ባለፈ ወደ ግንባር በመዝመት ለሀገር እና ለወገን ደማቅ ታሪክ በመስራት ስማቸውን በታሪክ መዝገብ ላይ ማኖርም እንዲሁ።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ  የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መንግስቱ ኡርጌ በበኩላቸው፤ ተቋሙ የተማረ ሰው ሃይል በማፍራት፣ በምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች ላይ  ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተለይ በዩኒቨርሲቲው የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በቅርቡ የሚከፈቱ አዳዲስ የትምህርት ፕሮግራሞችን ጨምሮ በ37 የድህረ ምረቃ ፕሮግራም ትምህርት ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ሀገሪቱ በጤናው ዘርፍ የምትፈልገውን የሰው ሃይል ለማፍራት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ተመራቂዎችም  በተሰማሩበት የሙያ መስክ  ጠንክረው በመስራት ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት  ያጋጠማትን ፈተና ለማለፍ  የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከተማራቂዎች መካከልም ዶክተር አብራሃም አለማየሁ በሰጠው አስተያየት፤አሸባሪው ህወሃት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል  በከፈተው ጦርነት በህዝብ እና በጤና ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን  ጠቅሶ፤ በተለይ የጤና ተቋማቱን መልሶ ለማደራጀት በሚከናወነው ስራ ላይ  በመሳተፍ  በሙያው ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

ኒያ አህመድ በበኩሏ፤  በተለይ ለጀግናው መከላከያ ሰራዊት ያላትን አክብሮት ገልጻ፤ በተመረቀችበት የሙያ መስክም ሀገሯንና ወገኗን ለማገልገል  ጠንክራ እንደምትሰራ አስታውቃለች።

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ  ዛሬ ካስመረቃቸው  መካከል 16 በስፔሻሊስት፣ ሶስት  በዶክትሬት ዲግሪ ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ በሁለተኛና የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ  መሆናቸውን በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም