በተገኘው ድል ሳንኩራራ በቀጣይ ሊያጋጥሙን ለሚችሉ ፈተናዎች ተግቶ መዘጋጀት ይገባል

97

ታህሳስ 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) በተገኘው ድል ሳንኩራራ በቀጣይ ሊያጋጥሙን ለሚችሉ ፈተናዎች ተግቶ መዘጋጀት እንደሚገባ የፌደራል ተቋማትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።

የፌደራል ተቋማትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሲያካሂዱ የነበረውን ውይይት አጠናቀዋል።

በዘመቻ ህብረ-ብሄራዊ አንድነት በተገኙ ድሎች፣ በታዩ ውስንነቶችና በቀጣይ ስለሚኖረዉ አቅጣጫ አስመልክቶ ባለፉት ሦስት ቀናት ውይይት ሲካሄድበት የቆየው የፌደራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ግምገማዊ ሥልጠና በዛሬው እለት ተጠናቋል።

ከፍተኛ አመራሮቹ በውይይታቸው በጦርነት የሚገኝ ድልን በአግባቡ መምራት ከጦርነቱ በኋላ ለሚመጣ መረጋጋትና ሰላም እንዲሁም ለዘላቂ የሀገር ግንባታ ሂደት ትልቅ ፋይዳ እንዳለዉ አስምረውበታል፡፡

በዘመቻውም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ድል ማድረጋቸውን አረጋግጠዋል፡፡የህልውና ዘመቻው ያስከተለዉ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት እጅግ አሳዛኝና የሀገር እዳ ቢሆንም ሂደቱ ግን በርካታ ትሩፋቶችን እንዳስገኘ አመራሩ ገምግሟል፡፡ተናብቦና ተቀናጅቶ በአንድ አመራር ለአንድ ዓላማ የመስራት አቅም፣ ህብረ-ብሄራዊ አንድነትና ሁለንተናዊ ህዝባዊ ተሳትፎና ተደጋግፎ ችግሮችን በጋራ መሻገርን እንዳስገኘ አመራሮቹ በግምገማ አዘል ስልጠናቸዉ አረጋግጠዋል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው አመራሮቹ ከድሎቹ ጋር የታዩና ቀጠይም ሊኖሩ ስለሚችሉ መልካም እድሎችና ዝንፈቶችን በትኩረት ገምግመዋል፡፡

በጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት በተካሄደው የማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ዘመቻ ለኅብረ ብሄራዊ አንድነት የመጀመሪያዉ ምእራፍ በስኬት እንዲጠናቀቅ ኢትዮጵያዊያን የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸው ለዚህም ላቅ ያለ ተሳትፎና አበርክቶ ምስጋና አቅርበዋል።

በተገኘው ድል ሳንኩራራ በቀጣይ ሊያጋጥሙን ለሚችሉ ፈተናዎች ተግተን መዘጋጀት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስብራቶች ለመጠገን የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስምረውበታል፡፡በየደረጃዉ ያለው አመራርም በጦርነቱ ጫና የደረሰበትን የብልፅግና ጉዟችንን ለማስቀጠል ታሪካዊ ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጽያዊያን በዘመቻው የተገኘውን የኅብረ ብሄራዊ አንድነት ስሜት በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባትና ሁለንተናዊ ብልጽግናችንን ለማረጋገጥ እንድንጠቀምበትም ጥሪ ማቅረባቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም