የሚዲያ ተቋማት የጥላቻ ድልድይን እያፈረስን የጠነከረች ኢትዮጵያን ለመገንባት መስራት አለብን

100

ታህሳስ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሚዲያ ተቋማት የጥላቻ ድልድይን እያፈረስን የጠነከረች ኢትዮጵያን ለመገንባት መስራት አለብን ሲሉ የሚዲያ ተቋማት ስራ አስፈጻሚዎች ገለጹ።

የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦቢኤን) በአሸባሪው ህወሓት ውድመት ለደረሰባቸው የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጣቢያዎችና ማዕከላት መልሶ መቋቋሚያ የሚሆን ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉን የተረከቡት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ምክትል ስራ አስፈጻሚ ሰጠኝ አቧሀይ አሸባሪው ህወሓት ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የጥቃት ኢላማ ካደረጋቸው ተቋማት መካከል አሚኮ አንዱ እንደነበር ጠቅሰዋል።

ለዚህም ማሳያው አሸባሪው ወረራ ፈጽሞባቸው በነበሩ አካባቢዎች የሚገኙትን የሚዲያውን መሠረተ ልማቶች ማውደሙ ምስክር መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ የደሴ ኤፍኤምን ወደ ስራ በመመለስ በአሸባሪው ተወረው በነበሩ አካባቢዎች የሚገኘውን ህብረተሰብ ስነ ልቦና መገንባትና ወደ ልማት መመለስ የተቋሙ ዋነኛ ትኩረት  ነበር ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፤ አሁን ደግሞ ኦቢኤን ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው ምስጋና አቅርበዋል።

ይህ አጋርነት በሁሉም ዘርፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት ምክትል ስራ አስፈጻሚው፤ የሚዲዎች መጠንክር የበለጸገች ኢትዮጵያን እንድናይ ይረዳናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሰፊ ሀብትና ጸጋ ያላት በመሆኑ ይህንን ሀብት ለመጠቀም ሚዲያዎች ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የኦቢኤን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዝናቡ አስራት በበኩላቸው አሸባሪው ህወሃት ህዝብን በትክክል የሚያገለግሉ ተቋማትን እንደማይፈልግ ተናግረዋል።

የወደሙ ተቋማትን በዚህ ጊዜ ማገዝና መደገፍ እንደሚገባ ገልጸው፤ “ዛሬ የመጣነው ጊዜ የማይሰጠውን የሚዲያ ስራ ልንደግፍ ነው“ ብለዋል።

የሚዲያ ተቋማት በጀግኖች አጥንትና ደም የተቋቋሙ ናቸው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ “የጥላቻ ድልድይን እያፈረስን የጠነከረች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚዲያ ድርሻ ወሳኝ በመሆኑ የግልና የህዝብ ተቋማት በአንድነት መስራት አለብን“ ብለዋል።

በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ እንድሪስ የአሸባሪውን እኩይ አላማ ከቀለበስን በኋላ የሚኖረው የሀገር ግምባታ ስራ ሰፊ ነው ብለዋል።

ለጠላቶቿ የማትበገር ኢትዮጵያን ለመፍጠርና በህብረተሰቡ መካከል ትስስርን ለማጠናከር የሚዲያው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ቀጣይ በሚናከወነው አካታች ውይይትም ሚዲያው በላቀ ብስለትና ጥበብ ሀሳቦች እንዲቀርቡ በማድረግ ታሪካዊ ሚናውን መጫወት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩላቸው “ሚዲያው ለህብረተሰቡ ድምጽ ተሰሚነት ከሌሎች ተቋማት በላይ ሚናው ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ወደ ልማትና የተሻለ ደረጃ እንዲሻገር ሚዲያው ትልቅ አቅም ስለሚሆን በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም