ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ግቡን እንዲመታ ከምሁራን ምክረ ሀሳብ ይጠበቃል

91

ሀዋሳ ፤ ታህሳስ 22/2014 (ኢዜአ) ሀገራዊ የሆነ የምክክር መድረኩ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ከማንኛውም አቋምና የግል ፍላጎት የፀዳ ምክረ ሀሳብ ማቅረብ ከምሁራን እንደሚጠበቅ የሀዋሳና ዲላ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አስገነዘቡ።

የሠላም ሚኒስቴር ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በብሔራዊ መግባባት ፣ በውጭ ጣልቃ ገብነትና በኢትዮጵያ የሠላም ፖሊሲ ላይ ያተኮረ  ውይይት ከ12 የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ምሁራን ጋር በቅርቡ  አካሂዷል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲና ልማት ፣ ጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን መምህርና ተመራማሪ ዶክተር መልሰው ደጀኔ ለኢዜአ እንዳሉት፤ አካታች ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ የሀገረ-መንግስት ግንባታ ላይ ሁሉም ዜጋ እንዲወያይና አሻራውን እንዲያኖር ያስችላል።

በሌላ በኩል የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር ገልጸው፤ አካታች ሀገራዊ ምክክሩ የታለመለትን ግብ እንዲመታ   ከአካባቢያዊነትና ግላዊ ምልከታዎች የፀዳ ገዢ ምክረ ሀሳብ ማቅረብ በየደረጃው ከምንገኝ ምሁራን ይጠበቅብናል ነው ያሉት ዶክተር መልሰው።

ዶክተር መልሰው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያዊያን ከውስጥና ከውጭ የተጋረጠባቸውን የህልውና አደጋና ጫና ለመመከት ልዩነቶችን ወደጎን በመተው በጋራ ሀገራዊ ጉዳያቸው ላይ አንድ ሆነው በመቆማቸው ታላቅ ሀገር መሆኗን አስመስክረዋል ።

በዚህ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ባይተዋርነት እንደማያስፈልግ ገልጸው፤ በየትኛውም የኢኮኖሚ ፣ ማህበራዊና ፣ ፖለቲካዊ ዘርፍና ደረጃ ላይ ያለ ሁሉም ዜጋ በያገባኛል መንፈስ በምክክሩ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት ነው ያመላከቱት።

በቀጣይም  በአካታች ሀገራዊ ምክክሩ የሁሉም ዜጎች ሀሳባቸውን በነፃነትና በእኩልነት የሚያንሸራሸሩበትና የተሻለ ሊያግባባ የሚችል ሀሳብ የሚፈልቅበት መሆን እንዳለበት ዶክተር መልሰው አመልክተዋል።

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ዳዊት ሀዬሶ፤ በኢትዮጵያ  በተካሄዱ የሥርዓት ለውጦች ውስጥ አዲስ የፖለቲካና አስተዳደር እሳቤ ይዞ ከመምጣት ባለፈ የሰፊውን ህዝብ ሀሳብ ያካተተ የሀገረ መንግሰት ግንባታ እንዳልተከናወነ ነው የተናገሩት።

እነዚህ የፖለቲካ ርዕዮቶችም ከማቀራረብ ይልቅ በአመዛኙ ህዝብን ከህዝብ በሚከፋፍሉና አብሮነትን በሚፈታተኑ ትርክቶች የተቃኙ እንደነበር ጠቅሰዋል።

ለማንም የማይበጁ የተዛቡ ትርክቶችን በውይይት  በማረም በተለይ ለድርድር የማይቀርቡ የጋራ ሀገራዊ አጀንዳዎችን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን የዳበረ የመመካከርና ችግሮችን የመፍታት ባህል አለን ያሉት ዶክተር ዳዊት ፤ሀገር በቀል እውቀቶቻችንና የሠላም እሴቶቻችንን ተጠቅመን መግባባት ላይ በመድረስ ጠንካራ ሀገር መገንባት እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።

በተለይ በሚፈጠሩ መድረኮች ላይ ሀገራዊ እውነታዎችንና ነባራዊ ሁኔታዎችን በምሁራዊ ዕይታ መተንተን እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ፤ለያዝነው ሙያ ታማኝ በመሆን ከግላዊ ፍላጎት የፀዳ ምክረ ሀሳብ በማቅረብ ህብረተሰቡን ማስገንዘብ ይጠበቅብናል ብለዋል።

በውይይቱ ስንሳተፍ ሁላችንም ሀገራችንን እያሰብን መሆን አለበት ያሉት ዶክተር ዳዊት ፤በአቻ ለአቻ ድል" ዊን ዊን " እሳቤ የምንተዋቸው ፍላጎቶች እንዲሁም በይቅርታና ምህረት ዘግተን የምናልፋቸው እውነታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ከወዲሁ መገንዘብ እንደሚያስፈልግ  ገልጸዋል።

ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ሁሉን አካታች የሆነ ሠላምና ሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ ያተኮረና  ለዚህም ነጻና ገለልተኛ ተቋም ለመመስረት በሂደት ላይ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በቅርቡ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

የምክክር መድረኩ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች እና ሀገረ-መንግስት ግንባታ ላይ  እንጂ ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር የሚደረግ ድርድር እንዳልሆነ ሊታወቅ እንደሚገባም በመግለጫው  ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም