በአዲስ አበባ የሕጻናት ዓይን ሕክምና ማዕከል ግንባታ ተጀመረ

110

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 22/2014(ኢዜአ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥር የሚገኘውን የሕጻናት ዓይን ሕክምና ማዕከል ግንባታ አስጀመረ።

የሕክምና ማዕከሉ ግንባታ በሦስት ዓመት እንደሚጠናቀቅና አንድ ቢሊዮን ብር ገደማ እንደሚፈጅ ተነግሯል።

በ2 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፈው ማዕከል 995 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ፣ በሦስት ዓመት እንደሚጠናቀቅና ለ150 ሺህ ሕጻናት ጥራቱን የጠበቀ የዓይን ሕክምና መስጠት እንደሚያስችል ተገልጿል።

በማዕከሉ ግንባታ ማስጀመሪያ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አመራሮችና የጤና ሚኒስቴር ተወካዮች ተገኝተዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዓይን ሕክምና ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ሳዲቅ ታጁ፤ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በጤናው ዘርፍ ጉልህ ሥራዎች ቢከወኑም በዓይን ሕክምና ላይ ብዙ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።

ከዓይን ጋር በተያያዘ ከሚከሰቱ ሕመሞች መካከል 90 በመቶው በቀላሉ ሊታከም የሚችል መሆኑን ገልጸዋል።

ነገር ግን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ እና በአፋር ክልሎች ምንም አይነት የዓይን ሕክምና መስጫ ማዕከላት አለመኖራቸው የሕጻናት ዓይን ሕክምናን አሳሳቢ እንዳደረገው ጠቁመዋል።

ዶክተር ሳዲቅ፤ ባለፉት 50 ዓመታት የዓይን ሕክምና ጥራትና ተደራሽነት በሚፈለገው ልክ አለማደጉንም ተናግረዋል።

የሕጻናት ዓይን ሕክምና ላይ ያለው ክፍተት ሰፊ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አማካሪ ዶክተር ሰለሞን ወርቁም ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ እንዲሳካ ሌሎች ከሚያደርጉት ተሳትፎ ባሻገር ሁላችንም በአንድ ልብ ሆነን በጽናት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል።

የማዕከሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ በየዓመቱ የሚኖረውን የቅበላ አቅም ለማሳደግ፣ ለምርመራ የሚወስደውን የጊዜ ቀጠሮ ለማሳጠርና የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ለማካሄድ ይረዳል ተብሏል።

የሕጻናት የዓይን ሕክምና ማዕከሉን ፕሮጀክት ሐሳብ ከግብ ለማድረስ የ"ጦቢያ ግጥምን በጃዝ" መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ምሥራቅ ተፈራ አምባሳደር በመሆን ተሾማለች።

ለሕክምና ማዕከሉ መጀመር አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም