በጎ አድራጊዋ ወይዘሮ አሸባሪው ህወሃት በአፋርና አማራ ክልሎች ላወደማቸው ሁለት ሆስፒታሎች መልሶ ግንባታ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፉ አደረጉ

229

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 22/2014(ኢዜአ) በበጎ አድራጎት የሚታወቁት ወይዘሮ ቦጋለች ከበደ አሸባሪው ህወሃት በአፋርና አማራ ክልሎች ላወደማቸው ሁለት ሆስፒታሎች መልሶ ግንባታ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፉ አደረጉ፡፡

በጎ አድራጊዋ ከዚህ ቀደም ለገበታ ለሀገር 1 ሚሊዮን ብር ፣ለሕዳሴ ግድብ 1 ሚሊዮን ብር ፣ ለመቄዶንያ 2 ሚሊዮን ብር እንዲሁም የመኖሪያ ቤታቸውን በመሸጥ ለመከላከያ ሰራዊት 2 ሚሊዮን ብር መለገሳቸው ይታወቃል፡፡

በዛሬው እለት ደግሞ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ለወደሙና በደሴ እና በአፋር ክልል ለሚገኙ ሁለት ሆስፒታሎች  መልሶ ግንባታ 3 ሚሊዮን ብር ለግሰዋል፡፡

ወይዘሮ ቦጋለች ድጋፉን ዛሬ ለጤና ሚኒስቴር ያስረከቡ ሲሆን በወቅቱም የገጠመንን ችግር በመረዳዳትና በመደጋገፍ ለማለፍ ሁላችንም የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

“ሁሉም የሚያምረው ሀገር ሲኖር ነው” በማለትም ነው የተናገሩት፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በአሸባሪው ቡድን የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

የግንባታ ሂደቱን በተመለከተ ከህብረተሰቡ ጋር በመደጋገፍና በመተባበር ከተሰራ በአጭር ጊዜ ውስጥ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን በመጠገን ለአገልግሎት ብቁ ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

ኀብረተሰቡ በአሸባሪው የህወሃት ቡድን በአፋርና አማራ ክልል የወደሙ የጤና ተቋማትን ስራ ለማስጀመር የሚደረገውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

ወይዘሮ ቦጋለችን ላበረከቱት አስተዋጽኦ በማመስገን የእውቅና ሰርትፊኬት አበርክተውላቸዋል።