የዳያስፖራ አባላት በአሸባሪው ህወሓት ወረራ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ እንቅስቃሴ ጀምረዋል

169

ታህሳስ 22/2014/ኢዜአ/ በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለመደገፍ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የዳያስፖራ አባላት ገለጹ።


የሽብር ቡድኑ ህወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች በፈፀመው ወረራ በርካታ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ሲፈናቀሉ ንብረታቸው በግፍ ወድሞባቸዋል፡፡

ተፈናቃዮችን ለማገዝና መልሶ ለማቋቋም የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ዳያስፖራውም ተግባራዊ ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል።

በደቡብ አፍሪካ ነዋሪ የሆኑትና የዩናይትድ ሚዲያ ሀውስ አስተባባሪ በኃይሉ መሃመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዚያ የሚኖረው ማኅበረሰብ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርግ እየተሰራ ነው።

በደቡብ አፍሪካ በሁሉም አካባቢዎች ገንዘብ እየተሰባሰበ መሆኑን ገልጸው ገንዘቡን ለታለመለት ዓላማ ለማዋል ሁኔታዎች እንደሚመቻቹ አክለዋል።

ለዚህም በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ምሁራን፣ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማኅበርና የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጋራ በመሆን ውጤታማ ተግባር እያከናወኑ ነው ብለዋል።

አቶ በኃይሉ “በጋራና በተባበረ ክንድ በመስራት የኢትዮጵያ ጠላቶች እንዲያፍሩ እናደርጋለን” ነው ያሉት፡፡

“ከኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ብርቅም ሀገሬ ከውስጤ አልወጣችም” ያሉት ደግሞ በአሜሪካ ቨርጂኒያ ነዋሪው ሰለሞን ኪዳኔ ናቸው።

ኢትዮጵያውያንን መልሶ ለማቋቋም ጥሪ ሲቀርብ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ገንዘብ ገቢ በማድረግ የድርሻዬን እየተወጣሁ ነው ብለዋል።

ከደቡብ አፍሪካ ደርባን የመጡት ፕሮፌሰር ዳምጠው ተፈራ በበኩላቸው በአማራና አፋር ክልሎች የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ዳያስፖራው ትርጉም ባለው ደረጃ እንዲሳተፍ መንግስት መስራት አለበት ብለዋል።