የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ መናበብ የአሸባሪውንና የውጭውን ጫና ዋጋ እያሳጣው ነው

202

እንጅባራ፤ ታህሳስ 22/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ መናበብ አሸባሪውና የአንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት ጫና ዋጋ እያሳጣ እኩይ ዓላማቸው እንዳይሳካ እያደረገው ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የእንጅባራ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ተናገሩ።


በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ አቶ አለምነህ አጋጄ በአንድ ሀገር መንግሥትና ህዝብ ተናበው ሲንቀሳቀሱ ለተሻለ ሀገር ግንባታና የውጭ ጣልቃ ገብነቶችን ለማክሸፍ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ በተግባር በመታየቱ አሸባሪው ህወሃት እና ተልዕኮ የሚያስፈፅምላቸው አንዳንድ ምዕራባውያን ኢትዮጵያን የማፍረስ ፍላጎታቸው ምኞት ሆኖ እየቀረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ዳያስፖራውን ጨምሮ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከጫፍ ጫፍ በሰው ኃይልና በሎጂስቲክስ በመነቃነቅ በጦርነቱ ድል እንዲመጣና ጫናውን እንዲቋቋም ማድረጉን አመላክተዋል።

“ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅመውን፣ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስከብርላትን እና ለሀገር ግንባታ ሁሉም በመተባበር ጦርነቱን መቋጨት፤ ሀገርንም ማሻገር ይገባናል” ነው ያሉት።

ቡድኑ ከአንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት ጋር እያደረገ ያለውን ሀገር የመበተን እኩይ ተግባር እስከ መጨረሻው ለማክሸፍ መንግስትና ህዝብ በተጀመረው አግባብ ተናበው መስራታቸውን መቀጠል አለባቸው ነው ያሉት።

በዩኒቨርሲቲው የህግ መምህር የሆኑት እንደገና አማረ በበኩላቸው፤ መንግስት አሸባሪ ቡድኑ ላይ የወሰደው እርምጃና አሁን የተከተለው አቋም የቡድኑን በራሱ የመጥፋት ዕድሉን በማፋጠን ህዝብና መንግስትን የበለጠ አንድ እንደሚያደርጋቸው አስረድተዋል።

መንግስት በሰብዓዊ እርዳታ ስም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችን በጥንቃቄ ማየት እንዳለበት የተናገሩት ምሁሩ፤ የኢትዮጵያ ወዳጅ ሀገራትን ማብዛትና ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ማጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል።