በመዲናዋ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የመጡ ዳያስፖራዎች እና ነዋሪዎች በጋራ የሚሳተፉበት ስፖርታዊ ሁነቶች ይካሄዳሉ

268

አዲስ አበባ፣  ታህሳስ 22/2014(ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ዳያስፖራውና የመዲናዋ ነዋሪዎች በጋራ የሚሳተፉበት ልዩ ልዩ ስፖርታዊ ሁነቶችን ሊያዘጋጅ መሆኑን ገለፀ።

የቢሮው ዋና ኃላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ስፖርታዊ ሁነቶቹ ዳያስፖራው ከመዲናዋ ኗሪዎች ጋር እየተዝናና የአንድነት ስሜቱን እንዲያጠናክር ይረዳሉ ብለዋል።

ከታህሣሥ 24 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በመስቀል አደባባይ ለአንድ ወር ያህል የከተማ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴና የማለዳ ስፖርት እንደሚደረግ ገልፀዋል።

በተጨማሪም የእግርኳስ ጨዋታ፣ የእግር ጉዞ ፣ የቴኒስና የውሃ ዋና ውድድሮች እንደሚደረጉም ነው የተናገሩት፡፡

ዲያስፖራው ከቅዱስ ጊዮርጊስና ከኢትዮጵያ ቡና ክለብ ከተውጣጡ ተጫዋቾች ጋር በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታ እንደሚያደርግ ጠቅሰው፤ ከጨዋታው የሚገኘው ገቢም ለአገር መከላከያ ሠራዊት እንደሚውል ተናግረዋል፡፡

“ለወገኖቼ ድጋፍ እሮጣለሁ” በሚል መሪ ሃሳብ  የ5 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ እንደሚከናወንና “ሽርሽር በሸገር” በሚል መርህ ደግሞ የመዲናዋን መዳረሻ ሥፍራዎች በብስክሌትና በፈረስ ግልቢያ ለመጎብኘት መታሰቡን ገልፀዋል።

በሌላ በኩል የገናን በዓል ምክንያት በማድረግም በመጪው ታህሣሥ 27 ቀን 2014 ዓ.ም የባህል ስፖርት ፌስቲቫል በጃንሜዳ ትምህርትና ሥልጠና ማዕከል እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

በዕለቱም 13ተኛው ከተማ አቀፍ የባህል ስፖርትና ውድድር ፌስቲቫል የመክፈቻ ፕሮግራም ይከናወናል ነው ያሉት አቶ አብርሃም ታደሰ።