የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ሀገራዊ የዳሰሳ ጥናት አካሂዷል

287

ታህሳስ 22/2014/ኢዜአ/ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን በአስተዳደር ወሰን፣ በማንነትና ራስን በራስ በማስተዳደር ዙሪያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ማወቅ የሚያስችል ሀገራዊ የዳሰሳ ጥናት ማካሄዱን ገለጸ።


ኮሚሽኑ ከሰኔ 2012 ዓ.ም ጀምሮ በአስተዳደር ወሰን፣ በማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጉዳዮች ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲያካሂድ የነበረውን ጥናትና ምርምር አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

ጥናትና ምርምሩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መሪነት ችግሮች ባሉባቸው አካባቢዎች የሚገኙ 28 የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተሳተፉበት ነው ተብሏል።

ኮሚሽነሩ ዶክተር ጣሰው ገብሬ እንደገለጹት በጥናቱ 68 ዞኖችና ልዩ ወረዳዎችን ለማካተት ቢታቀድም በጸጥታና በትብብር ማነስ በ12 ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ጥናት አልተደረገም።

ጥናቱ ሲከናወን የድርሳናት ዳሰሳ፣ የቁልፍ መረጃ ሰጪ ቃለ-ምልልስና ሌሎች የመረጃ መሰብሰቢያ አመራጮች ጥቅም ላይ ውለዋል።

በሀገራዊ ጥናቱ የትግራይ ክልል በድርሳናት ክለሳ መረጃ አሰባሰብ የተካተተ ቢሆንም የመስክ መረጃውን መሰብሰብ እንዳልተቻለ ገልጸዋል።

በጥናቱ ለአስተዳደር ወሰን፣ የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደርና የህግና ፖሊሲ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ችግሮች፣ ምክንያቶች፣ መንስኤዎችና ምክረ ሃሳቦች ተለይተዋል።

በቀረበው ሀገራዊ የጥናት ውጤት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግና ግብዓት በማሰባሰብ ለሚመለከተው አካል ምክረ-ሃሳቦችን እንደሚያቀርብ ገልጸዋል።

የጥናቱ ሰነዶች የማንነት፣ ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የአስተዳደር ወሰን እና የህግና ፖሊሲ አማራጭ ሰነዶች በሚል ለችግሮች የማያዳግም መፍትሄ እንዲሰጡ ተደርገው መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

በጥናቱ በፀጥታ ችግር ያልተካተቱ 12 ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በቤንሻንጉልጉሙዝ ክልሎች የተወሰኑ ቦታዎች ሲሆኑ በትብብር ማነስ ደግሞ በደቡብ ክልል የሚገኙ መሆናቸውን ዘርዝረዋል።

ጥናት ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች የሚመለከታቸው አካላት ለኮሚሽኑ ስራ የመተባበር ህጋዊ ግዴታ እንዳለባቸው አውቀው ለስራው ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹም አሳስበዋል።

በጥናቱ ከ70 በላይ ተመራማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ለ18 ወራት ሲካሄድ መቆየቱ፤ ከትግራይ ክልል በስተቀር ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከኮሚሽኑ ጋር በቅርበት የሚሰራ ተወካይ መመደባቸው ተነግሯል።

ኮሚሽኑ ከአስተዳደር ወሰን፣ ከማንነትና ራስን በራስ ከማስተዳደር ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ ለዘላቂ መፍትሄ ምክረ ሃሳብ እንዲያቀርብ በ2011 ዓ.ም የተቋቋመ ነው።