የወሎ ዩኒቨርሲቲ ከሶስት ወራት በኋላ ወደ መደበኛ መማር ማስተማር ስራ ይመለሳል

156

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) የወሎ ዩኒቨርሲቲ ከሶስት ወራት በኋላ ወደ መደበኛ መማር ማስተማር ስራ እንደሚመለስ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር አስታወቀ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ እንደተናገሩት፤ አሸባሪው ህወሃት በከባድ መሳሪያ በመታገዝ ጭምር በወሎ ዩኒቨርሲቲ 11 ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው ንብረቶችን አውድሟል፡፡ 

የህክምና፣ የተፈጥሮ ሳይንስና የምህንድስና ቤተ ሙከራዎችን ጨምሮ ከውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የተገነቡ ዘመናዊ የቴክኖለጂ ማዕከላት በአሸባሪ ቡድኑ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎችና የአይሲቲ መሰረተ ልማቶችን መዝረፉንና መውሰድ ያልቻላቸውን ደግሞ አገልግሎት እንዳይሰጡ አድርጎ ማውደሙን አብራርተዋል፡፡

የደረሰውን ወድመት መልሶ በመገንባት ዩኒቨርሲቲውን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችሉ ስራዎች መጀመራቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም የመማር ማስተማር ሂደቱ ከሶስት ወራት በኋላ በድጋሚ እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ከመጀመሪያ ዲግሪ አንስቶ አስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደነበር ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም