አሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ከ210 በላይ ንጹሃንን ገድለዋል፥ በሚሊዮኖች የሚያወጣ ንብረት ዘርፈዋል

146

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 22/2014(ኢዜአ) አሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ከ210 በላይ ንጹሃንን መግደላቸውንና በሚሊዮኖች የሚያወጣ ንብረት መዝረፋቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

በዞኑ የደረሰውን ውድመት መልሶ በማቋቋም በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ነው ያስታወቀው፡፡

የዞኑ የሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊና ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ኢንድሪስ በሰጡት መግለጫ አሸባሪ ቡድኖቹ በዞኑ ከ210 በላይ ንፁሃንን በግፍ ከመግደላቸው ባለፈ ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት መዝረፋቸውን ተናግረዋል፡፡

ዘርፈው መውሰድ ያልቻሉትን ማውደማቸውንም እንዲሁ፡፡

በዞኑ አሸባሪው ሸኔ አባላት የሚፈጥሯቸውን የፀጥታ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አሸባሪው ሸኔ  ለህወሃት የሽብር ቡድን ተላላኪ በመሆን እና መንገድ በመምራት በዞኑ በሚኖሩ ንፁሃን ዜጎች ላይ ግድያ፣ዘረፋና አስገድዶ መድፈር እንዲፈጽም ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

በዚህም በዞኑ በነዋሪዎቹ ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል ነው ያሉት፡፡

በዞኑ የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሸባሪው ሸኔን በማስወገድ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡