መጪውን የገና በዓል ስናከብር የተጎዱ ወገኖቻችንን በመደገፍ ሊሆን ይገባል

66

ታህሳስ 22/2014/ኢዜአ/ ሕብረተሰቡ መጪውን የገና በዓል ሲያከብር በቤት ውስጥ ያሉትን ትርፍ ቁሳቁስ ከመለገስ ጀምሮ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖቹን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ ጥሪ ቀረበ።

አሸባሪው የህውሓት ቡድን በወረራ በቆየባቸው የአማራና የአፋር ክልሎች በርካታ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለው ለችግር የተዳረጉ ሲሆን፤ በርካቶች ደግሞ ለዘመናት ያፈሩት ንብረት ወድሞባቸዋል፡፡

መንግሥት በችግር ወስጥ የሚገኙ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ስራ የጀመረ ሲሆን የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ትሳትፎ ይጠይቃል፡፡

ከዚህ አኳያ ወደ ቀያቸው የሚመለሱ ወገኖችን ለማቋቋም ከተጀመሩ የበጎ ፈቃደኞች እንቅስቃሴዎች ውስጥ ''የቤት እቃዬን ለወገኔ'' በሚል በተለያዩ ማሕበራዊ ሚዲያዎች የድጋፍ ማሰባሰብ ስራ ተጠቃሽ ነው፡፡

የበጎ ስራዎችን ከሚያስተባብሩ ግለሰቦች መካከል ወይዘሮ አያልሰው ወርቅነሕ እንደሚሉት፤ እንቅስቃሴው በችግር ወስጥ ለሚገኙ ወገኖች የማብሰያ ቁሳቁስ በማሰባሰብ በተወሰነ ደረጃ ከችግራቸው እንዲያገግሙ ማድረግን ያለመ ነው።

መጪውን የገና በዓል ስናከብር በችግር ላይ ያሉትን ወገኖች በመደገፍ ሊሆን ይገባል ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ አስተባባሪ ወይዘሮ ሀረግ እሸቱ ናቸው

እነዚህ ወገኖች ካሉበት ወቅታዊ ችግር አንጻር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የወገኖቻቸውን እገዛ እንደሚሹ በማንሳት፤ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች በዓሉን ተደስተው እንዲያከብሩ ለማድረግ መረባረብ እንደሚገባ ነው የገለጹት።

በአሁኑ ወቅት ማንኛውም ዜጋ የማይጠቀምበትና በትርፍነት ያስቀመጣቸውን የማብሰያ ቁሳቁስ በመለገስ የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም