ዳያስፖራው የኢትዮጵያን ጠላቶች በማጋለጥና በመቃወም በሀገራችን ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ አኩሪ ገድል ፈጽሟል

43


ሰመራ፤ ታህሳስ 22/2014(ኢዜአ) ዳያስፖራው የኢትዮጵያን ጠላቶች በውጭው ዓለም በማጋለጥና በመቃወም በሀገራችን ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ አኩሪ ገድል ፈጽሟል ሲሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ተናገሩ።


ርዕሰ መስተዳድሩ የተለያዩ ተቋማት በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የቡድኑን እኩይ ዓላማ በአጭሩ መቅጨት የተቻለው በሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጎች ርብርብ ነው።

ድሉ የተገኘው ከኢትዮጵያ ጥምር የፀጥታ ኃይሎች ተጋድሎ ጀርባ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ የቁርጥ ቀን ልጆች የሚችሉትን ሁሉ ጥረት በማድረጋቸው ነው ብለዋል።

በተለይም ዳያስፖራዎች ከሽብር ቡድኑ ጀርባ ተሰልፈው ሀገራችንን ለመበተን ሲያሴሩ የነበሩ የውጭ ጠላቶችን በማጋለጥና በመቃወም ከሀገራቸው ጎን ቁመው ታግለዋል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ።

አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባውያንና ሚዲያዎቻቸው በኢትዮጵያ ላይ የሚያራምዱትን ለሽብር ቡድኑ የወገነ አካሄድ በተለያዩ መድረኮች በአደባባይ ድምጻቸውን ማሰማታቸውን አመላክተዋል።

በዚህም ኢትዮጵያዊነት ድንበር የማይገድበው፤ በጊዜ ብዛት የማይደበዝዝ ብርቱ ማንነት መሆኑን አሳይተዋል ብለዋል።

ስለሀገራቸው ክብርና ሉዓላዊነት በአንድነት ቁመው በዚህ ወሳኝ ሰዓት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ለዓለም በማሰማት ኢትዮጵያን ያኮራ ገድል መፈጸማቸውን ተናግረዋል።

ታሪካዊ ተጋድሏቸውን ትውልድ ሲዘክረው የሚኖር ትልቅ ክብርና ምስጋና የሚቸረው አኩሪ ተግባር መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም