በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ ተቋማትን መልሶ የመገንባት ስራ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ኃላፊነት ነው

78

ታህሳስ 22/2014/ኢዜአ/ በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ ተቋማትን መልሶ የመገንባት ስራ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ኃላፊነት መሆኑን የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።


የሃይማኖት አባቶች ይህን ያሉት በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ከፍተኛ ውድመት የደረሰበትን የደሴን ሆስፒታል በጎበኙበት ወቅት ነው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶች እንዳሉት አሸባሪው የህወሓት ቡድን ከሰው ልጅ የማይጠበቅ እጅግ ጭካኔ የተሞላበት ግፍ ፈፅሟል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቦረና፣ የጉጂ እና የሊበን ዞኖች ሊቅ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሆኑት ብጹዕ አቡነ ዜና ማርቆስ፤ አሸባሪ ቡድኑ በሰው ልጆችና ንብረት ላይ እጅግ አሳዛኝ ግፍ መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም የሽብር ቡድኑ የህዝብ ሃብት በሆነው በደሴ ሆስፒታል ላይ ያደረሰው ጉዳት ለህዝብ ፈፅሞ የማያስብ ስብስብ መሆኑን ያመላከተ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት የሰላም እና ዘርፍ ኃላፊ ሼህ መሃመድ ሲራጅ፤ በደሴ ሆስፒታል በደረሰው ውድመት እጅግ ማዘናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ-ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዚዳንት ቄስ ዮናስ ይገዙ በበኩላቸው፤ የህዝብ መገልገያ ተቋማትን ማውደም ከሰው ልጆች የማይጠበቅ እና ሊፈጸም የማይገባ አስነዋሪ ተግባር እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የሃይማኖት አባቶቹ ባስተላለፉት መልዕክትም የወደሙትን ተቋማት መልሶ መገንባት የሁሉም የኢትዮጵያውያን ኃላፊነት መሆኑን በማንሳት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በመተባበር የተሻለ ነገን እንደሚገነባ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም