ሊያፈርሱት የሞከሩትን ሁሉ ያፈረሰ የኢትዮጵያ ክንድ

1016

ሊያፈርሱት የሞከሩትን ሁሉ ያፈረሰ የኢትዮጵያ ክንድ

  • የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በታሪክ ህዳጎች ሁሉ ባጋጠሙት ፈተናዎች ሳይበገር ደሙን እያፈሰሰ፣ አጥንቱን እየከሰከሰ፣ ለሰንደቁ ክብር፣ ለአገሩ ሉአላዊነትና ነጻነት በመስዋእትነት ተዋድቋል፤ ሀገሩንም ከፍ አድርጓል።
  • ኢትዮጵያ ጠሉ አሸባሪ ቡድን  በ1983 ዓ.ም በባዕዳን ተደግፎ ወደስልጣን ሲወጣ ቀዳሚ ተግባሩ ያደረገው የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት ስምና ዝና በማጉደፍ፣ ገድልና ታሪኩን በመካድ፣ ስሙን በማጠልሸት ሰራዊቱ እንዲበተን ማድረግ ነበር።
  • የጥቅምት 24 ቀን 2013 ጥቃት በርግጥም የቡድኑን አረመኔነት ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ብቻም ሳይሆን ቡድኑ ኢትዮጵያን እንደፈለገ ለማሽከርከር ካልቻለም ለመበተን አስቀድሞ የሚዘምተው የሀገር ምሳሌ የሆነ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ መሆኑን በግልጽ ያረጋገጠም ነበር።
  • መከላከያ ሰራዊቱ የተፈጸመበትን ክህደት ቀልብሶ የአሸባሪ ቡድኑን አገር የማፍረስ ተግባር እያከሸፈ በድል እየገሰገሰ መውጫ መግቢያ ሲያሳጣው የቀድሞውን ሰራዊት ‘የደርግ ሰራዊት’ እንደሚለው ሁሉ በሁለንተናዊ ሪፎርም ዳግም የተደራጀውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት “የአብይ ሰራዊት” በማለት የተለመደ የሴራ አካሄዱን ጀመረ።
  • አሸባሪው ህወሐት ኢትዮጵያን ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቸው የቀድሞ ሰራዊትን በትኖ የአንድነት መንፈስን ለማዳፈን ቢሞክርም አልተሳካለትም፤ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ሰሜን እዝ ላይ የጭካኔ በትሩን ቢያሳርፍም ኢትዮጵያን መበተን አልሆነለትም፤ ይህም ከህግ ማስከበር በሕልውና ዘመቻው በገሀድ የታየ ዕውነታ ነው።

ኢትዮጵያ ለዕልፍ ዓመታት ነጻነትና ሉዓላዊነቷ ታፍሮና ተከብሮ ኖሯል። ይህ ግን ዕድል አይደለም፤ ህዝቧ በየዘመናቱ የተፈራራቁ ውጫዊ ጠላቶችን ድባቅ እየመታ በድል የመዝለቁ ውጤት እንጂ። ለዚህም ይመስላል ታሪኳ የጦርነት ገፆች የበዙበት። ቅኝ ግዛት ያልበገራት አፍሪቃዊት አገር ኢትዮጵያ ነጻነቷን ሳታስደፍር የቆየችው በእምቢ ባይ ልጆቿ ወኔና የተባበረ ክንድ እንጂ ከሀያላኑ ጋር የሚተካከል የጦር መሳሪያ ስለታጠቀች አልነበረም። ዘመናዊ ጦር ሰራዊት ግንባታ የጀመረችውም ከረፈደ ነበር።

ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ውትድርና ስርዓት ጠንሳሽ ይሰኛሉ። በደመወዝ የሚተዳደር ወታደር ግንባታን አሃዱ ብለው ጀምረዋልና። ኢትዮጵያ ጠላተ-ብዙነቷን ተረድተው ከእንግሊዟ ንግስት የዘመናዊ ጦር መሳሪያ ድጋፍ ወይም ኢትዮጰያ ራሷን በቴክኖሎጂ እንድታበለጽግ ጦር መሳሪያ አምራች ጥበበኞች እንዲላክላቸው ጥረዋል። የኋላ ኋላ ለንጉሰ ነገሥቱ ሕልፈት መንስዔ የሆነው ጋፋት ላይ የተሞከረው የሴፓስቶፖል መድፍ ስሪትም አርቆ ከማሰብ ብርቱ መሻት የመነጨ ነበር። ዳሩ የእንግሊዝ ጦር በ1861 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ ሁሉም ከንቱ ሆኖ የቴዎድሮስ ህልም በአጭር ተቀጭቷል። ከዚያ ቀደም ብሎም ሆነ ከዚያ በኋላ በነበሩ ጦርነቶች (የአድዋን ጨምሮ) የሚዘምተው በብዛት የገበሬ ጦር ነበር።

ከዳግማዊ አጼ ቴዎድሪስ በኋሏም ዘመናዊ ጦር ግንባታ ጅማሮ የተስተዋለው በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል። ለዳግማዊ ምኒልክ ዘመናዊ ሰራዊት ግንባታ መነሻ የሆነውም አገር በቀል እውቀትን መሰረት ያደረገው የሃረር አሚሮች ከተማቸውን ከሰርጎ ገቦች ለመጠበቅ ያቋቋሙት ደወሪያ የተሰኘ የሰላም ጠባቂ ታጣቂ ሀይል እንደነበር ይነገራል። የሐረር ገዥ የነበሩት ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ከአሚሮቹ ልምድ በመቅሰም በሃረር ከተማ ዘመናዊ ፖሊስ ማቋቋማቸውን ተከትሎ ምኒልክም ይህ ልምድ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ አድርገዋል። ምኒልክ ወደ አዲስ አበባ ያስመጧቸው ሰላም ጠባቂዎችም የሰአት እላፊ ህግን የማስከበር አገልግሎት ነበራቸው። ቀጥሎም ከፖሊሶቹ ለየት ያለ “የመትረየስ ዘበኛ” የተባለ የጦር ክፍል ተቋቁሟል።  

የኢትዮጵያ ዘመናዊ የጦር ሰራዊት መሰረቱ በዚህ መልኩ ይሁን እንጂ በተደራጀና በይፋ ዘመናዊ መልክ ያለው የጦር ግንባታ የተጀመረው ግን ከፋሽስት ኢጣልያ ወረራ ቀደም ብሎ በቀዳማዊ አጼ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ስለመሆኑ ድርሳናት ያረጋግጣሉ። ክብር ዘበኛ የሚሰኘው ይህ ጦር በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ቢጨናገፍም ለዘመናዊ ጦር ሰራዊት መሰረት የሆነ፤ በወረራው ወቅትም በማይጨው ዘመቻ እና ጥቁር አንበሳ በሚሰኘው ጦር ስር አገራዊ ግዳጅና አርበኝነት የተወጣ ሰራዊት ነበር። ድሕረ ፋሸስት ወረራም ኢትዮጵያ ዘመናዊ ጦር ግንባታዋን አጠናክራ ቀጥላለች፤ ይህ ጦርም የወደፊቷ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እንዲከበር መሰረት የሆነ፤ ኮሪያና ኮንጎን መሰል ዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ግዳጆች ላይ በመሳተፍ ኢትዮጵያን ያኮራ፣ ስሟን ያስጠራ አብሪ ኮከብ ነበር። የኢትዮጵያን ግዛት አንድነት በማስጠበቅ፤ አገራዊ ሰላምና ጸጥታን በማስከብርም የክብር ዘበኛ፣ ምድር ጦር እና ፖሊስ ሰራዊት ሚናው የማይተካ ነበር።

የኢትዮጵያ መከላከያ ግንባታ በ1966ቱ አብዮት ከተገረሰሰው ዘውዳዊ መንግስት በኋላም በደርግ ወታደራዊ ዘመነ መንግስት ተጠናክሮ ቀጥሏል። በ1969 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ድጋፍ እስከ አፍንጫዋ ታጥቃ በእብሪት ኢትዮጵያን የወረረችውን ሶማሊያ መመከት የተቻለው ቀደም ብሎ በነበረውን የዘመናዊ ወታደር እርሾ መሰረት በማድረግ ነበር። በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ የጦር ሰራዊት ስልጠና አካሂዳ ወረራውን ቀልብሳለች። መደበኛ ሰራዊቱም ሆነ በታጠቅ ጦር ሰፈር የሰለጠነው የሚሊሻ ጦር ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ በመስዕዋትነት ታሪክ ሰርቶ አልፏል፤ አገርን ለቀጣይ ትውልድ አሻግሯል።

እናም የኢትዮጵያ ጦር ወይም መከላከያ ሰራዊት በታሪክ ህዳጎች ሁሉ ባጋጠሙት ፈተናዎች ሳይበገር ደሙን እያፈሰሰ፣ አጥንቱን እየከሰከሰ፣  ለሰንደቁ ክብር፣ ለአገሩ ሉአላዊነትና ነጸነት በመስዋእትነት ተዋድቋል፤ ሀገሩንም ከፍ አድጓል። ይህ በጀግንነት ለአገር የመዋደቅ ታሪኩ በየስርዓተ መንግስቱ የቀጠለ ነበር። በዚህም ውትድርና ለኢትዮጵያዊያን የተከበረና የሚያኮራ ሙያ በመሆኑ ውትድርናን ለመቀላቀል ወጣቶች የሚጎተጎቱበት አልነበረም። ምንም ስንኳ ደርግ የጀመረው ‘አፈሳ’ የተወሰነ ተጽዕኖ ቢያሳድርም።

እራሱን የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር /ትሕነግ/ በማለት የሚጠራው ኢትዮጵያ ጠሉ አሸባሪ ቡድን  በ1983 ዓ.ም በባዕዳን ተደግፎ ወደስልጣን ሲወጣ ቀዳሚ ተግባሩ ያደረገው የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት ስምና ዝና ማጉደፍ፣ ገድልና ታሪኩን መካድና ስሙን ማጠልሸት ነበር። መከላከያው በአሉታዊ መልኩ ተስሎ እንዲዋረድ ለማድረግ ብዙ ተሰርቷል። በዚህም ጨፍጫፊነት፣ አገር አፍራሽነት፣ አውዳሚነት… የወታደሩ ግብር ተደርጎ በተቃርኖ ተዘመተበት።

የወታደር ክብር የአገር ክብር ነውና ወታደሩ ሲካድና ሲዋረድ አገር ተካደች፤ ተዋረደች፤ አገርና ወገን ተበደለ። ሰራዊቱ ተበተነ። የቢሸፍቱው የጀግኖች አምባ፣ የዝዋይው ህጻናት አምባ ፈረሰ፡፡ የቀድሞ ሰራዊት ውለታው ርሀብ፣ እርዛት ሆኖ ለልመና ተዳረገ። በሞተላት ኢትዮጵያ ባይተዋር፤ ተመጽዋችና ስደተኛ ሆነ፡፡ በዓለም ላይ ጭራቅ በሚሰኘው የሂትለር ጦር እንኳ ሲሸነፍ አዲሱ የጀርመን መንግስት ጦሩን አልበተነም። ከአገሩ ዳር ድንበር አልፎ ተርፎ በኮሪያ፣ በኮንጎና በሌሎች ዓለም አቀፍ ዘመቻዎች የተሰለፈው የኢትዮጵያ ሰራዊት ግን እንዲበተን በአሸባሪው ህወሀት ተፈረደበት። ግማሽ ምዕተ ዓመታት የተደከመበት፣ ከድሃ ህዝብ ጉሮሮ ተቀንሶ የተገነባ ሰራዊት በአፍራሽ ኮሚቴ እንዲበተን ተደረገ።

ምክንያቱ ደግሞ የወያኔ ጥላቻ፣ እኩይ ዕቅድ እና ኢትዮጵያን የማፍረስ ሴራ አካል ሆኖ እናገኘዋለን። የቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ጀኔራል መኮንኑ ሜጀር ጀኔራል ጌታቸው ገዳሙ በአንድ ወቅት ለኢዜአ እንደተናገሩት ወያኔ ከመሰረቱ ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ስለሌለውና ዕቅዱም ኢትዮጵያን ማፈራረስ በመሆኑ ለዕኩይ ዓላማው ስኬት የቀድሞ ሰራዊት ሳንካ ይሆንብኛል ብሎ በመስጋቱ ማፍረስ ነበረበት። በምትኩም ዕኩይ ዓላማውን ያሳካልኛል ብሎ ያመነበትን በራሱ አምሳያ ቀርጾ መመስረት ፈለገ። የቀድሞው ጦር አባላት ሲበተኑም መብታቸው ተጠብቆ ሳይሆን ጡረታቸው ተከልክሎ፣ ሕክምና ተከልክለው፣ የዕድር ገንዘባቸው ሳይቀር ተነፍጎ ነው። ይህ ጭካኔም ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ካለው ጥላቻ የመነጨ ነው ይላሉ ጀኔራሉ። ጦሩን ብቻ ሳይሆን ህጻናት አምባ የነበሩ የተሰዉ ወታደሮች ህጻናት ልጆችንም ጭምር ሜዳ በመበተን የተበቀለ ከይሲ ቡድን ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት የድጋፍና የልማት ማሕበር ፕሬዚዳንት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ አሸባሪው ህወሐት ኢትዮጵያን ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቸው በጀግንነቱና አገር ወዳድነቱ የሚታወቀውን የቀድሞ ሰራዊት በትኖ የአንድነት መንፈስን ለማዳፈን ቢሞክርም ሙሉ ለሙሉ አልተሳካለትም ይላሉ። ይህም በሕልውና ጦርነት በገሀድ የታየ ዕውነታ ነው።

የህግ ባለሙያና ጠበቃ ወንድሙ ኢብሳ በአንድ ወቅት ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ “ላለፉት 150 አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ከስድስት ጊዜ በላይ ከባድ ወረራ የተፈጸመባት ቢሆንም አንዳቸውም  ከፖለቲካ ወይንም ከኢኮኖሚ ፍላጎት ባለፈ  እንደ ህወሃት ሃገር ለማፍረስ አልመጡም” ሲሉ የአሸባሪው ህወሃትን ሃገር ጠልነት ጥግ ገልጸውታል።

ጠንካራ መከላከያ ሰራዊት በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት ቅንጦት ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያም ምንም እንኳ ከረፈደ ብትጀምርም ብቁና ጠንካራ ሰራዊት ግንባታዋን ማጠናከር የጀመረቸው ከዚህ ሐቅ በመነሳት ነበር። ምክንያቱም በፖለቲካና በዲፕሎማሲ የማይፈታ አገራዊ ችግር የመጨረሻው የህልውና ማስጠበቂያ አማራጩ ጦርነት ነውና ጠንካራ የአገር መከላከያ ሰራዊት ግንባታ ጥያቄ ውስጥ አይገባም።  

አሸባሪው የሕወሃት ቡድን ስልጣን ላይ በወጣበት ቅጽበት የኢትዮጵያ ሕልውና የጀርባ አጥንት የሆነን፤ በአንዲት ደሃ አገር አንጡራ ሀብት ለ50 ዓመታት የተገነባን ሰራዊት በአሳፋሪ ሁኔታ የበተነው ይህ አውነታ ጠፍቶት እንዳልሆነ መረዳት ይቻላል። ይልቁኑም ሉዓላዊነቷና የግዛት አንድነቷን በማላላት ኢትዮጵያን የመበተን የመጨረሻ ግቡ እንዳይስተጓጎልበት በመሻት ነው።

በዚህም የሽብር ቡድኑ የግል ጥቅሙን ብቻ የሚያስከብር፣ ለውጭ ሃይሎች የሚያደገድግ፣  ሙስናን የባህሪ ገንዘቡ ያደረገ ስርዓት ለመገንባትና የበሰበሰ ስርዓቱን ለማስቀጠል በራሱ አምሳል ሌላ መከላኪያ ሰራዊት ለመገንባት ደክሟል። ይህንንም እውን ለማድረግ ለ27 ዓመታት ጥሯል። የአገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያዊነት መንፈስ እንዳይላበስ፣ ከአገር ይልቅ የዘረኝነት እሳቤ እንዲያጎለብት፣ ከአገር ህልውና ይልቅ ለሕወሃት ሕልውናው ዘብ እንዲቆም፣ ሰራዊቱ በህዝብ ዘንድ ታማኒ ተደርጎ እንዳይሳልና ክብር እንዳይኖረው በማድረግ አደራጅቷል።

ሰራዊቱ የሀገር ሳይሆን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዘብ እንዲሆን አድርጎታል። ይህ ቡደን የሰራዊትን መዋቅር በፖለቲካ እሳቤ በመቆጣጠር ሰራዊቱ ሕብረ ብሄራዊ ከመሆን ይልቅ በአሸባሪው ቡድን ከአንድ አካባቢ የተመለመሉ ጥቂቶች የሚዘውሩት አደረጃጀት እንዲኖረው አድርጓል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በህወሃት አገዛዝ ዘመን የነበረው የመከላከያ ሰራዊት ስብጥር ምን ያህል የተበላሸ እንደነበርና እርሱን ለማስተካከል እየተሰራ ይለውን ሪፎርም በተመለከተ በአንድ ወቅት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተናገሩትን ማስታወስ ያሻል።

ቀደም ሲል የነበረው የሰራዊቱ አደረጃጀት ህብረ ብሄራዊነትን ወደ ጎን የተወና አድሎአዊ ስለነበርም የኢትዮጵያ ሀዝብ በመከላከያ ሰራዊቱ እምነት፣ ባለቤትነት፣ ደጀንነት እና አለኝታነት ስሜት ሸርሽሮት ነበር። ወጣቶች ሰራዊቱን ወደውና አፍቅረው በወኔ እንዳይቀላቀሉ በትውልዱ ላይ የተዛባ ምስል እንዲኖር አድርጓል። ከዚህ ባለፈ በሰራዊቱ ውስጥ በሚደረገው ሻጥርና ጭቆና በርካታ የጦር መኮንኖችና ወታደሮች ሰራዊቱን እንዲለቁ፣ እንዲታሰሩ፣ እንዲገደሉና እንዲሰደዱ አድርጓል። እናም ሕወሃት እንኳን የቀድሞውን የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ቀርቶ በራሱ ዘመን እንኳ የተበቀላቸው መከላከያ ሰራዊት አባላት እልቆ-ቢስ ናቸው። ከ27 ዐመታት በኋላ የጦር ሰራዊት ሪፎርም ማድረግ ሲጀመር ክፉኛ የተቃወመው ይህ ቡድንም ስውር ጥቅሙና ሴራው ስለሚበጠስበት መሆኑን በመገንዘብ እንደሆነ እሙን ነበር።

ይህ ቡድን ከስልጣን ተግፍቶ በክልል በመሸገበት ወቅት እንኳን በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ በሰገሰጋቸው የአገር ክብር አዋራጅና ከሃዲ አመራሮቹ በራሱ ዘመን የተገነባን ሰራዊት ዳግም ክዷል። ጥቅምት 24 ቀን 2013 ጥቃት በርግጥም የቡድኑን አረመኔነት ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ብቻም ሳይሆን ቡድኑ ኢትዮጵያን እንደፈለገ ለማሽከርከር ካልቻለም ለመበተን አስቀድሞ የሚዘምተው የሀገር ምሳሌ የሆነ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ መሆኑን በግልጽ ያረጋገጠም ነበር። ጄነራል ጌታቸው ገዳሙ “እነዚህ 27 ዓመት ቆይተው ከክፉ መንገዳቸው ሊታረሙ ያልቻሉ አረመኔዎች ናቸው። እባብ እንኳን ቆይቶ ሰንኮፉን ይቀይራል። አብሯቸው የኖረ፤ ሬሽን አብሯቸው ሲቆርስ የነበረን ሠራዊት ነው በግፍ የገደሉት። ጭካኔያቸው ምንም መለኪያ የለውም” ነበር ያሉት በወቅቱ።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን በመልሶ ማጥቃት ድል መደረግ ሲጀምር የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን ስሙን እንኳ መጥራት አልፈቀደም። መከላከያ ሰራዊቱ የተፈጸመበትን ክህደት ቀልብሶ የአሸባሪ ቡድኑን አገር የማፍረስ ተግባር እያከሸፈ በድል እየገሰገሰ መውጫ መግቢያ ሲያሳጣው የቀድሞውን ሰራዊት ‘የደርግ ሰራዊት’ እንደሚለው ሁሉ በሁለንተናዊ ሪፎርም ዳግም የተደራጀውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት “የአብይ ሰራዊት” በማለት የተለመደ የሴራ አካሄዱን ጀመረ።

ሰሚ ግን አላገኘም። ምክንያቱም ዛሬ ትላንት አይደለም። ሰራዊቱ የማን እንደሆነ ህዝቡ በሚገባ ያውቃል። ለዚህም ነው ወጣቱ በሁሉም አቅጣጫ ሰራዊቱን ለመቀላቀል የተመመው። ይህን የሀገር አለኝታ መቀላቀል ትልቅ እድል መሆኑን ከተረዳ ውሎ አድሯል።  ኢትዮጵያ ሕልውናዋ የሚዘልቀው በጠንካራ ወታደራዊ አቅም ነውና ሰራዊቱን በመቀላቀል ወጣቱ እያሳየ ያለውን ተነሳሽነት አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል።

ጠላት ወደደም፤ ጠላም የአሸባሪውንና የጋላቢዎቹን ቅስም የሚሰብር፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ደጀንነነት የሚደገፍ ሰራዊት ተደራጅቷል፤ እየተደራጀም ይገኛል። የኢትዮጵያ አፍራሾች ይፈርሳሉ፤ ለዓመታት ኢትዮጵያዊያንን የመከራ ጽዋ ሲያስጎነጩ የነበሩ ከሃዲዎች ተዋርደው፤ ጎስቋላ ታሪክ ታቅፈው ይከስማሉ። በባንዳና ከሃዲዎች መቃብር ላይም ጠንካራ የኢትዮጵያ ወታደር ይነግሳል። የኢትዮጵያዊነት ፍም ከተዳፈነበት ምድጃ ዳግም ተቀጣጥሎ ፋናው ይወግጋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በኢትዮጵያዊነት መልክና ቀለም ተቀምሮ በሙያው እና ትጥቁ ዘምኖ፣ በዘመን አፈራሽ ቴክኖሎጂዎች ሁለንተናዊ አቅሙንና አንድነቱን አጎልብቶ ከአገሩ አልፎ ለአፍሪካ ኩራትና ደጀን ሰራዊት መሆኑን ይቀጥላል።