ከአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት የመጡ ኢትዮጵያዊያን 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ

144

ታህሳስ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት የመጡ ኢትዮጵያዊያን 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።

በተመሳሳይ ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ያሉ ዲያስፖራዎች ይዘወት የመጡትን የህክምና ግብዓት ለጤና ሚኒስቴር አስረክበዋል።


የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አንድ ሚሊዮን ዲያስፖራ በገና በዓል ወደ ሀገር እንዲገባ ጥሪ ማድረጋቸውን ተከትሎ በመላው ዓለም የሚገኙ  ዳያስፖራዎች ወደ ኢትዮጵያ እየጎረፋ ይገኛሉ።

ከ40 ዓመታት በላይ ነዋሪነታቸውን በአሜሪካ ሎስአንጀለስ ካሊፎርኒያ ግዛት ያደረጉት አቶ ነብዩ ኢሳያስ እና አቶ መርዕድ ተድላ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት መግባታቸውን ይናገራሉ።

አቶ ነብዩ ኢሳያስ እና አቶ መርዕድ ተድላ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ባዶ እጃቸውን ሳይሆን በካሊፎርኒያ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ያሰባሰቡትንና 5 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የህክምና ቁሳቁስ ይዘው ነው።

ድጋፍንም ለመከላከያ የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄነራል ቡልቲ ታደሰ እና ለጤና ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ተገኔ ረጋሳ አስረክበዋል።

ድጋፉም በዋናነት ለመከላከያ የጤና ተቋማትን ግብዓት ለማሟላት እንደሚውሉም ነው የተገለጸው፡፡

ዳያስፓራዎቹ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለመከላከያ ሰራዊት ትልቅ ክብር እንዳላቸውና በቀጣይም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ስለመሆናቸው ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ቆይታቸው ምን እንደሚያስፈልግ በመመልከት በቀጣይ በተደራጀ መልኩ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ነው የተናገሩት፡፡

የመከላከያ የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄነራል ቡልቲ ታደሰ በበኩላቸው ዳያስፖራው ለሰራዊቱ እያደረገው ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፤ ይህም ሰራዊቱ ግዳጁን በብቃት እንዲወጣ የሞራል ስንቅ እንደሚሆነው ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪን ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ያሉ ዳያስፖራዎች የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶችን ለጤና ሚንስቴር አስረክበዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ  ዛሬ ማለዳውን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ዳያስፖራዎች ይዘውት የመጡትን የህክምና ግብዓት ተረክበዋል።

ከ33 ዓመታት በላይ ኑሯቸውን በኖርዌይ ያደረጉት ወይዘሮ ራሄል እሸቴ ከባለቤታቸው ጋር በመሆን ለህክምና ግብዓት የሚሆኑ ቁሳቁሶችን እና 3 ሺህ ዶላር ድጋፍ አድርገዋል።

ከግሪክ አቴንስ የመጡት ሌላኛው ዳያስፖራ ቀሲስ ሰለሞን ገብረመድህን በግሪክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የላኩትን የህክምና ቁሳቁስ ይዘው በመምጣት ድጋፍ አድርገዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው የዳያስፖራው ማህበረሰብ አገራቸውን ለመደገፍ እያደረጉ ስላሉት ርብርብ ምስጋና  አቅርበው፤ ድጋፉ በቀጣይነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም