በአምስት ወራት ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ ባሉ ባንኮች ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ተቀማጭ አድርገዋል

220

ታህሳስ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) በዘንድሮ በጀት ዓመት የመጀመሪያ አምስት ወራት ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ ባሉ ባንኮች ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተቀማጭ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ዳያስፖራው በአገር ውስጥ ባሉ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ የሂሳብ ቁጥር ከፍቶ ገንዘብ ተቀማጭ የማድረግ ባህሉን እያሳደገ መጥቷል።

በዚሁ መሰረት በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት አምስት ወራት ከ2 ሺህ 303 ዳያስፖራዎች በአገር ውስጥ በሚገኙ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ የሂሳብ ቁጥር በመክፈት 1 ነጥብ 44 ሚሊዮን ዶላር ተቀማጭ ማድረጋቸውን ኤጀንሲው ለኢዜአ ገልጿል።

በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት 6 ሺህ 914 ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ የሂሳብ ቁጥር ከፍተው 7 ነጥብ 54 ሚሊዮን ዶላር ተቀማጭ ማድረጋቸውንም አስታውሷል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው የውጭ ምንዛሬ የሂሳብ ቁጥር ከፍተው ገንዘብ ተቀማጭ ማድረጋቸው የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን ከማበረታት አኳያ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

ዳያስፖራው ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ የሂሳብ ቁጥር ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትና ለውጭ ምንዛሬ ክምትች መጨመር ቁልፍ ሚና አለው።