በተለያዩ ሶስት ከተሞች ዘመናዊ የኦክስጂን ማምረቻ ማዕከላት ይቋቋማሉ

65

ሚዛን ታኅሣሥ 22/2014 (ኢዜአ) የጤና ሚኒስቴር በዚህ ዓመት ሶስት ዘመናዊ የኦክስጂን ማምረቻ ማዕከላትን ለማቋቋም እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ማዕከላቱ የሚገነቡት  በጋምቤላ፣ ነቀምቴና ቦንጋ ከተሞች መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቦንጋ ከተማ ለሚገነባው የኦክስጅን ማምረቻ  ትላንት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

በውይይቱ ላይ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተወካይ አቶ ወንዳፍራሽ ሚሊዮን እንደገለጹት በዚህ ዓመት ከሚቋቋሙት የኦክስጂን ማምረቻ ማዕከላት ውስጥ አንዱ የሚቋቋመው በቦንጋ ገብረ ጻድቅ ሻዎ አጠቃላይ ሆስፒታል ውስጥ ነው።

ማዕከሉ በሆስፒታሉ ይታይ የነበረውን የኦክስጅን እጥረት የሚቀርፍ መሆኑን አመላክተዋል ።

በሆስፒታሉ ከኦክስጅን ማምረቻ ግንባታ በተጓዳኝ ህጻናት፣ አዋቂዎችንና ድንገተኛ ታካሚዎችን በሚያስተናግዱ ዘመናዊ የህሙማን አልጋ እንደሚደራጅ ገልጸዋል።

ማእከሉን የማቋቋም ስራን በአጠረ ጊዜ በማጠናቀቅ አገልግሎት ለማስጀመር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከሆስፒታሉ አመራሮች ጋር ለመምከር መድረኩ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

ለሶስቱም ዘመናዊ የኦክስጂን ማምረቻ ማዕከላት የዲዛይን ጥናት ሥራ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን አቶ ወንዳፍራሽ አስታውቀዋል።

የቦንጋ ገብረ ፃዲቅ ሻዎ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቅረማርያም ጳውሎስ በበኩላቸው ሆስፒታሉ ባጋጠመው የኦክስጅን እጥረት ሳቢያ ለህሙሟን የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት ሲቸገር መቆየቱን አውስተዋል።

በተለይ ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የኦክስጅን ፍጆታ ይስተዋል እንደነበር ጠቅሰው አሁን የሚገነባው የኦክስጅን ማምረቻ ችግሩን እንደሚያቃልል ተናግረዋል።

ከሆስፒታሉም ባለፈ በአጎራባች ለሚገኙ የጤና ተቋማት ጭምር እፎይታን እንደሚሰጥ ስራ አስኪያጁ አመላክተዋል።

የጤናውን ዘርፍ በአንድ እርምጃ ወደ ፊት የሚያራምደው የማእከላቱ ግንባታ ሥራ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ተገቢው ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

ዘንድሮ የሚካሄደው ሦስት የኦክስጅን ማምረቻ ማዕከላት ግንባታ የሚከናወነው በጤና  ሚኒስቴሩና በልማት አጋሮች ትብብር እንደሆነ በውይይት ወቅት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም