የተገኘውን ሰላም በመጠቀም የህዝባችንን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ልንተጋ ይገባል

186

ሀዋሳ፤ ታህሳስ 22/2014 (ኢዜአ) በህልውና ዘመቻ የተገኘውን አንፃራዊ ሠላምና መረጋጋት በመጠቀም የህዝባችንን የልማትና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ልንተጋ ይገባል ሲሉ የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ አሳሰቡ።


የክልሉ ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር አንደኛ የሥራ ዘመን አንደኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል።

አፈ ጉባኤዋ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት፤ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ሲዳማም እንደሌሎች ወንድም ህዝቦች ልጆቹን ወደ ግንባር  በመላክ ሀገራዊ ግዴታውን ተወጥቷል።

የህልውና ዘመቻውን ለማጠናከር ለመከላከያ ሰራዊቱና ለሌሎችም በግንባር ለተሰለፉ የጸጥታ ሃይሎች የሚያስፈልገውን የስንቅ ፣ የገንዘብና የሞራል ድጋፍ በማድረግ የሀገር አለኝታነቱን በተግባር ማረጋገጡን አውስተዋል።

በተባበረ የኢትዮጵያዊያን ክንድ አሸባሪውን ህወሓት በወረራ ከያዛቸው የአማራና አፋር ክልሎች ጠራርጎ ማስወጣት እንደተቻለ ጠቅሰው፤ ይህንን ሀገራዊ ዘመቻ ማሳካት እንደተቻለ ሁሉ በቀጣይም ወደ ልማት በመመለስ መትጋት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በተለይ አሁን ላይ የተገኘውን አንፃራዊ ሠላምና መረጋጋት በመጠቀም ወደ ተጀመረው የብልጽግና ጉዞ ሳንታክት በመስራት የህዝባችንን ፍላጎት ለማሟላት መረባረብ ይጠበቅብናል ሲሉ አሳስበዋል።

የምክር ቤቱ ጉባኤ በቆይታው የስድስተኛ ዙር መስራች ጉባኤን ቃለ ጉባኤ፣ የክልሉን መንግስት የአስር  ዓመት መሪ ዕቅድ ፣ የምክር ቤት የአባላት ሥነ-ምግባር ደንብ እንዲሁም የሕግ አውጪ ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈፃሚ አካላትን የ2014 ዓ.ም በጀት ዕቅድ ላይ ተወያይቶ እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል።