የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ በደቡብ ወሎ ዞን በአሸባሪው ሕወሃት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ምግብ ነክ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

86

ታህሳስ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በደቡብ ወሎ ዞን በአሸባሪው ሕወሃት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ምግብ ነክ የሆኑ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ።

የጉባኤው የበላይ ጠባቂ አባቶች በደቡብ ወሎ በአሸባሪው ቡድን ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማትም ጎብኝተዋል።

ድጋፉን አስመልክተው አስተያየታቸውን የሰጡት የጉባኤው ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ አሸባሪው ህወሓት ባደረሰው ጥፋት በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጎድተዋል ሲሉ ገልጸዋል።

“ጉዳት የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች መልሶ የማቋቋም ስራም የሁላችንም የኢትዮጵያውያን ተግባር ነው” ያሉት ጠቅላይ ጸሐፊው፤ “ለዚህም በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍል የሚውል 300 ኩንታል ዱቄት እና 600 ካርቶን ማኮሮኒ ድጋፍ አድርጓል” ብለዋል።

ለወደፊቱም ሁሉም የእምነት ተቋማት የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ውስጥ የየራሳቸውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በድጋፍ ርክክቡ የተገኙት የኢትዮጵያ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ እንዳሉት የሃይማኖት ተቋማት ምዕመናቸውን አስተባብረው ለተጎዱት ወገኖች ድጋፍ ማድረግ ይገባቸዋል።

የሃይማኖት ተቋማት በጉባኤው በኩል ያደረጉት ድጋፍም የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ በበኩላቸው በአሸባሪው ቡድን ጉዳት የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የማቋቋም እና ድጋፍ የማድረግ የሁሉም የኢትዮጵያውያን ግዴታ ነው ብለዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መሳይ ማሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት ድጋፉ በጦርነቱ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚውል ነው፡፡

በደቡብ ወሎ በጦርነቱ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ለረሃብ መዳረጋቸውን ገልጸው፤ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ያደረጉት ድጋፍ ለእነሱ ይውላል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖች በአጠቃላይ 6 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የምግብ ነክ ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም