የድህረ-ጦርነት ማገገሚያ ስራዎች የስነ-ልቦና ድጋፍን ጨምሮ በሁሉም መስክ ያሉ ባለሙያዎችን ተሳትፎ ይጠይቃል

124

አዲስ አበባ ታህሳስ 22/2014(ኢዜአ) የድህረ-ጦርነት ማገገሚያ ስራዎች የስነ-ልቦና ድጋፍን ጨምሮ በሁሉም መስክ ያሉ ባለሙያዎችን ተሳትፎ እንደሚጠይቅ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን መምህርና ተመራማሪ ገለፁ።

አሸባሪው ህወሓት በወረራ ይዟቸው በቆየባቸው የአማራና አፋር ክልል አካባቢዎች ህፃናትን ጨምሮ በርካታ ንፁሃን ዜጎችን በግፍ ጨፍጭፏል፤ ሴቶችን ደፍሯል፤ በርካቶች ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ለችግር እንዲጋለጡ አድርጓል፡፡

የሽብር ቡድኑ የመሰረተ ልማትና ማሕበራዊ ተቋማት እንዲሁም ከተሞች እንዲወድሙ ከማድረጉ በተጨማሪ በፈፀማቸው የተለያዩ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች በዜጎች ላይ የስነ-ልቦና ጠባሳን ጥሎ አልፏል።

በአሁኑ ወቅት በአሸባሪው ቡድን የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ የማቋቋምና የመገንባት ስራ በመንግስትና በሀገር ወዳድ ዜጎች አማካኝነት እየተካሄደ ይገኛል።

የመልሶ ማቋቋሙ ስራ ከገንዘብና የቁስ ድጋፍ ባሻገር የስነ-ልቦና እገዛን ታሳቢ ያደረጉ መሆን እንዳለባቸውም ምሁራን ይናገራሉ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ደመላሽ መንግስቱ፤ አሸባሪ ቡድኑ ከፈጸመው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ባሻገር በዜጎች ስነ-ልቦና ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ነው ያሉት።

አሸባሪ ቡድኑ ኢትዮጵያዊያን ኃይማኖተኛ ህዝብ መሆናቸውን እያወቀ ቤተ እምነቶችን አውድሟል፤ ቁርዓንና መጽሃፍ ቅዱስ አቃጥሏል ነው ያሉት፡፡

ይህን ያደረገውም በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የሞራል ስብራት ለመፍጠር መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

በመሆኑም ዜጎች የሽብር ቡድን ካደረሰው የስነ-ልቦና ቀውስ እንዲወጡ ከሚደረጉ ድጋፎች መካከልም የሕክምናና የባለሙያ ድጋፍን ጨምሮ ሁሉን አቀፍ ሊሆን እንደሚገባም አንስተዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በተለይም በአርሶ አደሮች ላይ የፈፀመው ሰቆቃና ግፍ በእጅጉ የከፋ በመሆኑ የሁሉንም መስክ ባለሙያዎች ድጋፍ እንደሚሻ ነው የገለፁት።

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ የሚደረጉት የድህረ ጦርነት ማገገሚያ ስራዎች  የስነ-ልቦና ድጋፍን ጨምሮ በየመስኩ ያሉ ባለሙያዎችን ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑንም ነው ጨምረው የገለጹት፡፡