ዳያስፖራው በአምስት ወራት ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር ቤት ልኳል

140

ታህሳስ 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዳያስፖራው በዘንድሮ በጀት ዓመት አምስት ወራት ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ (ሬሚታንስ) በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር ቤት መላኩን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት አምስት ወራት ዳያስፖራው 1 ነጥብ 64 ቢሊዮን ዶላር ወደ አገር ቤት በሕጋዊ መንገድ መላኩን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በበጀት ዓመቱም አራት ቢሊዮን ዶላር ከሬሚታንስ ለመሰብሰብ መታቀዱን አመልክቷል።

ዳያስፖራው በ’አይዞን ኢትዮጵያ’ የገንዘብ ማሰባሰቢያ አማራጭ እና በውጭ አገራት በሚገኙ ሚሲዮኖች አማካኝነት ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል።

በ’አይዞን ኢትዮጵያ’ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ256 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ (ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር በላይ) ገንዘብ ከ23 ሺህ በላይ ዳያስፖራዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች መሰብሰቡ ተጠቁሟል።

ዳያስፖራው በአምስቱ ወር ለአገር መከላከያ ሰራዊት ከ103 ሚሊዮን ብር በላይ በገንዘብና በአይነትና ለገጽታ ግንባታ ስራዎች ደግሞ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ነው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ያስታወቀው።

በአምስት ወራቱ በኢንቨስትመንትና ንግድ ላይ ለመሰማራት የ22 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 339 ዳያስፖራዎች ፍላጎት ማሳየታቸውን አመልክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በነሐሴ ወር 2012 ዓ.ም ይፋ ላደረጉት የ’ገበታ ለአገር’ ፕሮጀክትም ዳያስፖራው ከ29 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ተጠቅሷል።

ከገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪ ዳያስፖራው ባለው ሙያ የእውቀት፣ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተመልክቷል።

የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ለኢትዮጵያ ልማትና እድገት እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የገለጸው ኤጀንሲው፤ የዳያስፖራው ሁለንተናዊ ንቁ ተሳትፎ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።

ዳያስፖራው ባለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት 9 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር ቤት መላኩን ኢዜአ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።