አሸባሪውን በህብረት በመመከትና ተጎጂዎችን በመደገፍ የታየው ተሳትፎ በመልሶ ግንባታም መጠናከር ይኖርበታል

145

ሰመራ፤ ታህሳስ 21/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሃት ቡድንን በህብረት በመመከትና ተጎጂዎችን በመደገፍ ኢትዮጵያዊያን ያሳዩት ተሳትፎ በቀጣይ በመልሶ ግንባታም መጠናከር እንዳለበት የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ ተናገሩ።

የተለያዩ ተቋማት በአፋር ክልል በአሸባሪው ጥቃት ለተፈናቀሉ ወገኖች  14ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ግምት ያላቸው  የምግብና ሌሎች  ቁሶች  ድጋፍ አድርገዋል።

ድጋፉን የተረከቡት ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት፤  በሽብር ቡድኑ የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍ በኩል ሁሉም ዜጋ የሚያኮራ ህብረት አሳይቷል።

ይህ አጋጣሚ ኢትዮጵያውያን የቆየ የመረዳዳትና የአብሮነት ባህላቸውን ዳግም ያደሱበት  መሆኑን ገልጸዋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን ከውጭ ጠላቶች ጋር በማበር  በሀገር ላይ የደቀነውን  አደጋ በተባባረ ክንድ በመመከት ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደማይቻል በተግባር አሳይተነዋል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

የሽብር ቡድኑን በህብረት በመመከትና ተጎጂዎችን በመደገፍ  ኢትዮጵያዊያን ያሳየነው ብርቱ ተሳትፎ  በቀጣይ  መንግስት በሚያከናውናቸው የመልሶ ግንባታም ላይ ማጠናከር ይኖርብናል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ድጋፉን  ካደረጉት ተቋሞች መካከል በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ህብረት-ሎጀስቲክስ መምሪያ  የህዝባዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል የመቶ አለቃ ሙሴ ሌራ እንደተናገሩት፤ ሠራዊቱ ሀገርና ህዝብን ከጠላት ከመጠበቅ  ባለፈ በሽብር ቡድኑ የተጎዱ ወገኖቹን የመድገፍ ሃላፊነቱን ለመወጣት ድጋፍ አድርጓል።

በዚህም  ከ9 ነጥብ 1ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ  የተለያዩ አልባሳት፣ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሶችና ምግብ አበርክተዋል።


ሌላው ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ ሃይል ሰጪ የሆኑ ብስኩቶችን ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ያደረገው  የጭላሎ ፉድ ኮምፕሌክስ ምክትል ስራ አስኪያጁ አቶ ከማል ደክሲሶ  በበኩላቸው፤ ለተጎጂዎቹ  የሚደረገውን ድጋፍ አጠናክረው ለመቀጠል ቃል ገብተዋል።

የአርሲ እና የመቱ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር   የሚገመት ለምግብነት የሚውል ድጋፍ  ለተፈናቀሉ ወገኖች አበርክተዋል።

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ  በጊዜያዊነት  ከ800  ሺህ ብር በላይ የሚገመት የምግብና አልባሳት ድጋፍ አድርጓል።

የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ አመሃ ዳኘ እንዳሉት፤ የአፋር ህዝብ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ የፈጸመው  ጀግንነት የተሞላበት ተጋድሎ የሽብር ቡድኑ እኩይ ዓላማ ለማክሸፍ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል ።

ለዚህም ከፍተኛ አክብሮት እንዳላቸው ገልጸው፤ ፓርቲው የክልሉ መንግስት በሚያከናውነው የመልሶ ግንባታ ስራዎች የሚጠበቅበትን እንደሚወጣም አስታውቀዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ተቋሞቹ ላደረጉት ድጋፍና ወገናዊ አጋርነት በክልሉ መንግስትና ህዝብ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
   

በአፋር ክልል በህወሃት አሸባሪ ቡድን ወረራ ምክንያት ከ377 ሺህ በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ተመልክቷል።