በድህረ ጦርነት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በጥናት ላይ ተመስርቶ ለመፍታት ከወዲሁ መዘጋጀት ይገባል

234

ታህሳስ 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከድህረ ጦርነት ጋር ተያይዞ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በጥናት ላይ ተመስርቶ ለመፍታት ከወዲሁ መዘጋጀት እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት የድህረ ግጭት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂደዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የማሕበራዊ ሳይንስ መምህር ዶክተር ታዬ ንጉሴ ለውይይት መነሻ ጽሁፍ ባቀረቡበት ወቅት በጦርነቱ ምክንያት የደረሰው የሰው ህይወት መጥፋትና መፈናቀል እየፈጠረ ያለው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ጫና ቀላል የማይባል እንደሆነ አብራርተዋል።

በመሆኑም ሊገጥሙ የሚችሉ ቀውሶችን ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ ለመፍታት ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል።

ቀውሱ የሚያስከትላቸው ችግሮች አለመረጋጋት እንዳይፈጥሩ ችግሮቹን ለመፍታት የሚያስችል ጥናት ከወዲሁ መካሄድ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

እንደ ዶክተር ታዬ ገለጻ፤ ከጦርነት በኋላ በሚከሰቱ ቀውሶች ለሚመጡ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍትሔን ለማበጀት በቅድሚያ ጥናት ማካሔድ ወሳኝ ተግባር ነው።

ለዚህ ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር መስራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።

የችግሩ ቀጥተኛ ሰለባ በሆኑ ወገኖች ዘንድ የሥነ ልቦና ቀውስ መፈጠሩ አይቀሬ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ በዩኒቨርስቲው የስነ-ልቦና ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ሀብታሙ ወንድሙ ናቸው።  

“ሰዎች የተወሰነ ያህል ተስፋ መቁረጥ ይመጣባቸዋል” ያሉት ፕሮፌሰር ሀብታሙ፤ ወገኖች የደረሰባቸውን ጉዳት ለማከም ተገቢ ጥናት ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ጉዳት ያጋጠማቸውን ሴቶችን፣ አረጋዊያንን፣ ልጆችን፣ ወጣቶችንና አዋቂዎችን ለብቻ ለብቻ በመለየት ችግሮቻቸውን ለመፍታት መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

የሃይማኖትና የጤና ተቋማት ሕዝቡን የማረጋጋት ስራ ላይ ትኩረት አድርገው ሚናቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም ነው የተናገሩት፡፡      

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼