በክልሉ የወሳኝ ኩነት የምዝገባ ሥራን ለማዘመን የሚያስችል የ”ኦን ላይን” የምዝገባ አገልግሎት ሊጀመር ነው

141

ጎንደር ፤ ታህሳስ 21/2014(ኢዜአ) በአማራ ክልል የወሳኝ ኩነት የምዝገባ ሥራን ለማዘመን የሚያስችል የ”ኦን ላይን “የምዝገባ አገልግሎት በመጪው ጥር ወር እንደሚጀምር የክልሉ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

ኤጀንሲው ከአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በትብብር ለመስራት በሚያስችለው የመግባቢያ ሰነድ ላይ ዛሬ በጎንደር ከተማ መክሯል፡፡

በመድረኩ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት መአዛ በዛብህ እንደተናገሩት፤ ኤጀንሲው የ”ኦን ላይን” የምዘገባ አገልግሎቱን ለመጀመር ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር እየሰራ ነው፡፡

ቴክኖሎጂው ዜጎች አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ኤጀንሲው መምጣት ሳያስፈልጋቸው ባሉበት በኦን ላይን ምዝገባ መረጃዎችን በመሙላት ማናቸውንም አገልግሎት የሚያገኙበት ዘመናዊ አሰራር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ቴክኖሎጂው በተለይም ቀደም ሲል ይካሄድ በነበረው የምዝገባ ስርዓት ዜጎች በተቋማት ኩነቶችን ሲያስመዘግቡ ይስተዋል የነበረውን ክፍተት እንደሚያስተካክል አስረድተዋል።

ኤጀንሲው አገልግሎቱን ለመጀመር የሚያስችለውን የባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ጨምሮ የዲጂታል የመረጃ ቋት ቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን የማደራጀትና የመትከል ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡

የኦን ላይን የምዝገባ አገልግሎቱን ጥር / 2014 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ በይፋ በማስጀመር በቀጣይም በጎንደር፣ በደሴና በሌሎችም የክልሉ ትላልቅ ከተሞች ለማስፋት መታቀዱን አስታውቀዋል።

የህወሓት የሽብር ቡድን በክልሉ በምስራቅ አማራ በፈጸመው ወረራና በኤጀንሲው ቅርንጫፎች ላይ በፈጸመው ዝርፊያ የአገልግሎት አሰጣጡ ሙሉ በመሉ መቋረጡንም ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የተቋረጠውን አገልግሎት መልሶ ለማስጀመር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ነው ወይዘሪት መአዛ ያመለከቱት ።

በክልሉ ባለፈው ዓመት በተካሄደ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ከ300 ሺህ በላይ ኩነቶችን መመዝገብ እንደተቻለም አመላክተዋል።

“የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ለዜጎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን ለመቅረጽ፣ እቅዶችን ለማዘጋጀት እና ስትራቴጂ ለመንደፍ ቁልፍ መሳሪያ ነው” ያሉት ደግሞ የክልሉ ፍትህ ቢሮ ሃላፊና የኤጀንሲው ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ገረመው ገብረጻዲቅ ናቸው፡፡

የወሳኝ ኩነቶች መዝገባ ውጤታማ እንዲሆንም የባለድርሻ አካላት ትብብርና ቅንጅታዊ አሰራር መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።

የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባል አባ ስንታየሁ ሙላው በበኩላቸው፤ የሃይማኖት ተቋማት ከኤጀንሲው ጋር በትብብር መስራታቸው ህብረተሰቡ የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኝ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

“የተቋማቱ አብሮ መስራት የልደት፣ የጋብቻ እና የሞት መረጃዎችን ከሃይማኖት ተቋማትም በቀላሉ አሰባስቦ በየጊዜው ለኤጀንሲው በመላክ ክልላዊ መረጃዎችን በአግባቡ መዝግቦና አደራጅቶ ለመያዝ ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል” ብለዋል፡፡

ኤጀንሲውና የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው በቀጣይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

በመድረኩ ከምስራቅና ምዕራብ ጎጃም፣ ከአዊ፣ ከሰሜን፣ ከደቡብ፣ ከማዕከላዊና ከምዕራብ ጎንደር ዞኖች እንዲሁም ከጎንደር ከተማ የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የኤጀንሲው የሥራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡