ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ጉዳዮች በእጅ አዙር ጫና ሊፈቱ አይችሉም

66

አዲስ አበባ ታህሳስ 21/2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ጋር በቀጥታ በመወያየት እንጂ በእጅ አዙር ጫና ሊፈቱ እንደማይችሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ በሚኒስቴሩ የተከናወኑ የተለያዩ ተግባራት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የሚኒስቴሩ የ100 ቀናት ስራ አፈፃፀም ግምገማ መካሄዱንና በዚህም ተቋማዊ የመዋቅር ለውጡ ስኬታማ ሆኖ መጠናቀቁን ገልፀዋል።

ባለፉት ሶስት ወራት ዳያስፖራው እንዲንቀሳቀስና የውጭ ጫናው እንዲረግብ በማድረግ ረገድ ፍሬያማ ስራዎች እንደተከናወኑም በመጠቆም ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በመዲናዋ በተከናወነው የዳያስፖራ ማህበረሰብ አቀባበል መርሃ-ግብር ላይ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን በአሸባሪው ህውሓት የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ጠቅሰዋል።

ወደ አገር ቤት እየገቡ ላሉ የዳያስፖራ ማሕበረሰብ አባላት ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ዲፕሎማሲያዊ ይዘት ያላቸው መርሐ ግብሮች እንደሚከወኑም ነው የገለጹት፡፡

በጦርነት የተጎዱ ስፍራዎችን መጎብኘት፤የስጦታ መርሐ ግብር፣ የኪነ ጥበብ፣ የዳያስፖራ ፎረም፣ የስፖርት ክዋኔዎች፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ ገናን በላልይበላ ፣ጥምቀትን በጎንደር፣ የሚሊዮኖች ጉዞና ደም ልገሳ ከመርሐ ግብሮቹ መካከል ይገኙበታል።

በተጨማሪም የዳያስፖራ የድሕረ ግጭት ሚና፣ የኢንቨስትመንት ፎረም፣ ዳያስፖራ እንደ ወላጅና የምስጋና ፕሮግራሞችም እንደሚኖሩ ነው የተገለፀው።

የሚሊዮኖች ወደ አገር ቤት ጉዞም ዓመቱን ሙሉ እንደሚቀጠል ገልጸው፤ የገና ክብረ በዓልን ምክንያት በማድረገም እንግዶች በብዛት እየገቡ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም ጠንካራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ በመመስረት ረገድም በኢትዮጵያ በሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዳዲስ የትምህርት ክፍሎች እየተከፈቱ መሆኑን ቃል አቀባዩ አንስተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ኃይል በደቡብ ሱዳን እየተወጣ ላለው ተልዕኮ በተመድ ዓለም አቀፍ አድናቆት እንደተቸረውም አንስተዋል።

ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ለኢትዮጵያ ጠበቃ በመሆን የታገለችው ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ ሰሞኑን ወደ አገር ቤት እንደምትገባም ገልጸዋል።

ወደ አገር ቤት ለሚገቡ ሚሊዮኖች ቆይታቸው በፀጥታም ሆነ በሌሎች ሁኔታዎች የተሳካ እንዲሆን በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልፀው፤ ዳያስፖራው ያለምንም ማቅማማት ወደ አገር ቤት እንዲመጣ ጥሪ አቅርበዋል። 

የአሜሪካ ባለስልጣናት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በቀጥታ መወያየት ሲጠበቅባቸው ወደ ተለያዩ አገራት በመመላለስ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ጫና እያደረጉ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

የአሜሪካ ባለስልጣናት ከዚህ ቀደም በኬንያ፣ ሴኔጋል፣ ናይጄሪያ፣ ግብጽ፣ ቱርክና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መመላለሳቸወን አስታውሰዋል።

የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንም ከትናንት በስቲያ ከኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር መወያየታቸውን ገልፀዋል።

"አሜሪካ መወያየት ከፈለገች ኢትዮጵያ ሁሌም ዝግጁ ናት" ሲሉም ነው ያነሱት፡፡

በአሁኑ ወቅት በሶማሊያ ባለስልጣናት መካከል ያለው ሽኩቻ እና በሱዳን የተቀሰቀሰው ግጭት የአፍሪካ ችግር በአፍሪካ መፍትሔ በሚለው መርህ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ኢትዮጵያ ጽኑ ፍላጎት እንዳላትም በመግለጽ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም