የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አገር የማፍረስ ተልዕኮ ተቀብለው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ተልእኮ ለማምከን አስተዋጾ እያበረከተ ነው

234

ሶዶ፣  ታህሳስ 21/2014 ( ኢዜአ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አገር የማፍረስ ተልዕኮ ተቀብለው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ተልእኮ ለማምከን አስተዋጾ እያበረከተ መሆኑን የወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ እዝ ኮሚቴ አስታወቀ።

የኮሚቴው ሰብሳቢ መቶ አለቃ በየነ ባንጋ ለኢዜአ እንደገለፁት በከተማው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም አበረታች ውጤት እያመጣ ነው ።

በከተማው ከሰላማዊ ህዝብ ጋር በመመሳሰል እኩይ ዓላማቸውን ለመፈፀም የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች መኖራቸውን ተናግረዋል ።

“አዋጁ የሀገሪቱን ህገመንግስት በመጣስ ከጠላት ጋር በማበር ሀገር ለማፍረስ የሚሰሩ ግለሰቦችን በመለየት ለህግ በማቅረብ ረገድ አበረታች ውጤት አስገኝቷል ” ብለዋል።

በተለይም የአሸባሪው ህወሃትን ሀገር የማፍረስ  ዓላማ ለማሳካት ተልእኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ አግባብ እየተጣራ መሆኑን አመልክተዋል ።

“ግለሰቦቹ በተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገጾች የሀሰት መረጃ በማሰራጨት የሀገር ጠላቶችን በድብቅ እንደሚደግፉ  በጥቆማና በክትትል ተደርሶባቸዋል” ያሉት ሰብሳቢው  ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በምርመራ ሂደት ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ተያይዞ የተነሱ ክልከላዎች ቢኖሩም ለወንጀል መፈፀሚያ ሊውሉ የሚችሉ ባለሁለትና ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች የሰዓት ገደብ አለመነሳቱን ሰብሳቢው አስታውቀዋል።

በሶዶ ከተማ የሆቴል ጥበቃ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ተፈራ ያና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሀገር ለማፍረስ ለሚንቀሳቀሱ አካላት ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር የሚረዳ በመሆኑ ስራቸውን በዛ አግባብ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

”ህብረተሰቡ ውስጥ ተደብቀው ድብቅ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚጥሩ ፀጉረ-ልውጦች በስራዬ ሲያጋጥሙኝ በማጋለጥ ለሀገሬ ሰላም ዘብ እቆማለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም መንግስት ለሀገር ሰላም ይጠቅማል ብሎ የሚያወጣቸውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ጨምሮ ሌሎች መመሪያዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።