ግብረሰናይ ድርጅቱ ለጋምቤላ ክልል ሦስት አምቡላንሶችን ድጋፍ አደረገ

ጋምቤላ ፤ታህሳስ 21/2014 (ኢዜአ) "አይ አር ሲ" አለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት በጋምቤላ ክልል መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን ለማጠናከር የሚያግዙ ሦስት አምቡላንሶችን ድጋፍ አደረገ።

International rescue committee ወይንም ‘‘አይ አር ሲ’’ ያበረከታቸው አምቡላንሶች ከ5 ሚሊዮን 948 ሺህ ብር በሚበልጥ ወጪ የገዛቸው መሆኑም  ዛሬ በተካሄደው የርክክብ ስነ-ስርዓት ላይ ተገልጿል።

ድርጅቱ ከአውሮፓ ህብረት ባገኘው  የገንዘብ ድጋፍ ያበረከታቸው ሶስቱ አምቡላንሶች በክልሉ መሰረታዊ የጤና እና የሪፈራል የህክምና አገልገሎትን ለማጠናከር የተበረከቱ መሆናቸው ተመልክቷል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አምቡላንሶቹን በተረከቡበት ወቅት እንዳሉት"ድርጅቱ ያደረገው ድጋፍ የክልሉን የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት ያግዛል"።

ድርጅቱ በክልሉ ለጀመራቸው የጤና ልማት ስራዎች ውጤታማነት የክልሉ መንግስት ሁለንተናዊ ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ ለተደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።

አምቡላንሶቹ ለታለመላቸው አገልግሎት እንዲውሉ የክልሉ ጤና ቢሮ አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር እንዲያደርግም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ጊሎ በበኩላቸው፤ አምቡላንሶቹ ለማህበረሰቡ ፈጣንና መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን ለማዳረስ  የጎላ ፋይዳ አላቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም