ድርጅቱ ለምዕራብ ጉጂ የድርቅ ተጎጂዎች ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ

199

ነገሌ፣ ታህሳስ 21/2014(ኢዜአ) የኢጣሊያ መንግሥት በጎ አድራጎት ድርጅት በምእራብ ጉጂ ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ።

የዞኑ አደጋ ስጋት ሥራ አመራርና የልማት ተነሺዎች ጽህፈት ቤት እንደገለጸው ቼንትሮ አዩቲ ፕር ኢትዮጵያ የተሰኘው ድርጅት ለተጎጂዎቹ የሚውል 7 ሺህ 500 ኩንታል በቆሎ ድጋፍ አድርጓል፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ኢዮብ ዘሪሁን ለኢዜአ እንዳስታወቁት ድጋፉ በመልካ ሶዳ፣ በሱሮ በርጉዳ፣ በገላና፣ በአባያ፣ በቡሌሆራና በዱግዳ ዳዋ ወረዳዎች በድርቅ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እየተከፋፈለ ነው፡፡

በዞኑ በድርቅ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ እንዲጠናከር ተጠይቋል።

ድርጅቱ በቆሎውን ጉዳቱ ወደ ደረሰባቸው አካባቢዎች ለማጓጓዝ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡  

በዞኑ የበልግ ዝናብ የሚጀምረው በመጋቢት አጋማሽ በመሆኑ የምግብና የእንስሳት መኖ እጥረት ሳይባባስ ድጋፍ እንዲደረግ ኃላፊው ጠይቀዋል፡፡

በዞኑ ድርቅና በጸጥታ ችግር የተፈናቀሉ ከ300 ሺህ በላይ የአርብቶ አደር ቤተሰብ አባላት ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን አመልክተዋል፡፡

በዞኑ ድርቅ ተባብሶ በቀጠለባቸው ሶስት ወረዳዎች በመኖና በመድኃኒት እጥረት ከ8 ሺህ በላይ የቤት እንስሳት መሞታቸውንና 18 ሺህ 384 የቤት እንስሳት ደግሞ በሞት አፋፍ ላይ እንደሚገኙ አቶ ኢዮብ አስታውቀዋል፡፡