አሸባሪው ህወሓት በቤተሰቦቻችን ላይ የፈጸመው ጭካኔ የተሞላበት ግድያ ሕይወታችንን አመሰቃቅሎታል

194

ታህሳስ 21/2012/ኢዜአ/ ”አሸባሪው ህወሓት በቤተሰቦቻችን ላይ የፈጸመው ጭካኔ የተሞላበት ግድያ ሕይወታችንን አመሰቃቅሎታል” ሲሉ በሽብር ቡድኑ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ የራያ ቆቦ ከተማ እናቶች ይናገራሉ።

የሰሜን ወሎዋ ራያ ቆቦ ከተማ የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን የጭካኔ እጆች ካረፉባት ከተሞች መካከል አንዷ ናት፡፡

የሽብር ቡድኑ አባላት በዚሁ ከተማ ከእናትና ልጅ ነጥሎ የቤተሰብ አባ ወራዎችን ገድለዋል፣ ያለ ርህራሄ እህት እያየች ወንድም፤ ውንድም እያየ ደግሞ እህት ረሸነዋል፡፡

ኢዜአ በከተማዋ በመገኘት በአሸባሪ ቡድኑ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ እናቶችን አነጋግሯል።

ተጎጂዎቹ አሸባሪው ቡድን በከተማው በቆየባቸው ጊዜያት በነዋሪዎች ላይ እጅግ ዘግናኝ ግፍና ሰቆቃ መፈጸሙን ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።

በአሸባሪው ቡድን ባለቤታቸውን ከተነጠቁት መካከል ወይዘሮ ሰርኬ ፈንቴ የአሸባሪ ቡድኑ ታጣቂዎች ቤታቸውን አንኳክተው ካስከፈቱ በኃላ ባለቤታቸውን አስገድደው ከቤት ውስደው እንደገደሉት ይናገራሉ፡፡

“እሱን የት ነው ይዛችሁት የምትሄዱት እኔን ግደሉኝ እያልኳቸው፤ እኔን በመሳሪያ አስፈራርተው ባለቤቴን እንደሚታረድ በግ አንጠልጥለው ይዘውት ከአጠገቤ ተሰወሩ” ሲሉም የሽብር ቡድኑን ታጣቂዎች የጭካኔ ጥግ ይገልጻሉ።

ከባለቤታቸው ጋር በትዳር ሁለት ልጆች ማፍራታቸውን የጠቀሱት ተጎጂዋ ”ባለቤታቸውን ከአካባቢው አርቀው በጥይት እንደገደሉት” በምሬት ተናግረዋል።

ሌላኛዋ ተጎጂ ወይዘሮ ፋንታነሽ ምስጋን የአሸባሪው ቡድን ታጣቂዎች ወንድማቸው ስራ ውሎ በመመለስ ላይ እያለ በራቸው ላይ በጥይት እንደገደሉት ነው የሚናሩት።

”የአሸባሪው ቡድኑ ታጣቂዎች ለሰው ልጆች ፍጹም ርህራሄ የላቸውም” ያሉት ወይዘሮ ፋንታነሽ፤ በቤተሰባቸው ላይ በደረሰው ጉዳትም የወንድማቸውን ሁለት ልጆች የማሳደግ ኃላፊነት እሳቸው ላይ መውደቁን ተናግረዋል።

የአሸባሪ ቡድኑ ታጣቂዎች በከተማዋ በቆዩባቸው ጊዜያት የከተማዋ ነዋሪዎች ያሳለፉት ሰቆቃ አስከፊ እንደነበርም ነው ተጎጂዎቹ የሚናገሩት፡፡

የፌደራል የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት ከተማዋን ከአሸባሪ ቡድኑ ነጻ ማውጣቱ እጀግ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፤

በቀጣይም ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የራያ ቆቦ ከተማ የአገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ አበራ ንጉሴ በከተማዋ እስከፊ ሁኔታዎች ማዬታቸውን ይናገራሉ።

የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች በከተማዋ በቆዩባቸው ቀናት በቀን ከሁለት መቶ በላይ አስከሬን የተቀበረበት ጊዜ እንደነበርም ነው ያስታወሱት፡፡

አሁን ላይ አካባቢው ከሽብር ቡድኑ ነጻ በመሆኑ የደስታና የሰላም አየር እየተነፈሱ እንደሆነም ገልጸዋል።

በዚህ ወቅት የራያ ቆቦ ከተማ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ትገኛለች።