ኢትዮጵያን ለማፍረስ ግልፅ ወረራ ያካሄደውን አሸባሪው ህወሐትን በተባበረ ክንድ አንገትን ማስደፋት ተችሏል

150


ሀዋሳ፤ ታህሳስ 21/2014.(ኢዜአ) “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውጭ ጋላቢዎቹና ከውስጥ ተላላኪዎቹ ጋር ተማምሎ ግልፅ ወረራ ያካሄደውን አሸባሪው ህወሐትን በተባበረ ክንድ አንገትን ማስደፋት ተችሏል” ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ተናገሩ።

የሲዳማ ክልል ልዩ ኃይል የደንብ ልብስ በአዲስ መተካቱ ይፋ ተደርጓል።

በመርሃ ግብሩ ላይ አቶ ደስታ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውጭ ጋላቢዎቹና ከውስጥ ተላላኪዎቹ ጋር ተማምሎ ግልፅ ወረራ ያካሄደውን አሸባሪው ህወሐትን በተባበረ ክንድ አንገትን ማስደፋት ተችሏል።

አሁን ላይ የአሸባሪው ርዝራዥ ከአማራና አፋር ክልል በወረራ ከያዛቸው ቦታዎች ጠራርጎ በማስወጣት የህልውና ዘመቻውን የመደምደሚያ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ የሲዳማ ክልልና ህዝብ የቀጠናውን ሰላምና ደህንነት በንቃት ከማስጠበቅ ባለፈ ኢትዮጵያ በምትፈልገው አግባብና ቦታ በመሰለፍ ተልዕኮውን በአግባቡ መወጣት የሚችል ኃይል የማቅረብ ሀገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝም አቶ ደስታ አስታውሰዋል ፡፡

ክልሉ በቀጣይም አሸባሪው ህወሐት ከውስጥና ከውጭ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በማበር የሚቀጣውን ማንኛውም የሽብር ተልዕኮ ለመመከትና  ለመቀልበስ እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።

የፀጥታ አካላት የሚሰጣቸውን ክልላዊና ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ እንዲሆኑ ያሳሰቡት ርዕስ መስተዳድሩ፤ ለሕገመንግስታዊ ሥርዓት  መከበር በጽናት በመቆም የህዝቡን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ አበክረው  ሊሰሩ እንደሚገባም አመልክተዋል።  

ከክልሉ የፀጥታ አባላት መካከል ሀምሳ አለቃ ሺብሬ ጂሎ በሰጡት አስተያየት፤  ከሲዳማ ክልል ባሻገር  ሀገራችን ኢትዮጵያ በምትፈልገን ወቅት በየትኛውም ቦታ ተሰልፈን ግዳጅ ለመወጣት ዝግጁ ነን ብለዋል።

ምክትል ሳጅን መክሊት ጉጆ በበኩላቸው፤ የሲዳማ ልዩ ኃይል አባላት ብንሆንም የምንቆመው ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በየትኛውም ቦታ ተመድበው ለእናት ሀገራቸው ኢትዮጵያ ለመዋደቅ ዝግጁ እንደሆኑ ነው ምክትል ሳጂን መክሊት ያረጋገጡት ።