ያገኘነው ድል ዘላቂ የሚሆነው ብልፅግናን ለማረጋገጥ ከሰራንበት ብቻ ነው

183

ሀዋሳ፣ ታህሳስ 21/2014 (ኢዜአ) በአብሮነት ቆመን ጠላቶቻችንን በማሳፈር ያገኘነው ድል ዘላቂ መሆን የሚችለው ብልፅግናን ለማረጋገጥ ከሰራንበት ብቻ ነው ሲሉ የደቡብ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው ተናገሩ።

“ከህልውና ትግላችን ወደ ብልፅግና ጉዟችን” በሚል መሪ ሀሳብ  የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሀዋሳ ከተማ እየተወያዩ ነው።

ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ መድረክ እንዳሉት፤ መንግስት ሀገሪቱ ለዘመናት  ከነበረችበት ግጭትና የጦርነት አዙሪት እንድትላቀቅ ሁሉንም አካላት ባሳተፈ መልኩ ጥረት ጀምሯል።

በተለይ በዜጎች አንድነትና ህብረት ሀገሪቱን ወደ ብልጽግና ማማ እንድተሸጋገር ድፍረት የተሞላበት ውሳኔና እርምጃ መውሰዱንም አወስተዋል።

በዚህም ከለውጥ ማግስት ጀምሮ  በአጭር ጊዜ ውሰጥ ተአምራዊ እንቅስቃሴ በመደረጉ  ተዳፍኖና ደብዝዞ  የነበረው ኢትዮጵያዊነት ዜጎች ማዜም መጀመራቸውን ገልጸዋል።

 ይህ ያልተዋጠላቸው የውስጥና የውጭ ጠላቶች ኢትዮጵያን በኃይል በማፈራረስ  የሀገሪቱን ብሩህ ተስፋ ለመንጠቅ በሚችሉት አቅም ሁሉ መንቀሳቀሳቸውን አስረድተዋል።

በዚህም ተገደን የገባንበትን ጦርነት ድል አድርገናል ብለዋል።

መላው ኢትዮጵያዊያን የመከቱት ይኸው  የህልውና ጦርነት ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ የማይደራደሩና አንድ አቋም ያላቸው ህዝቦችመሆናችንን ዛሬም እንደትናንቱ  ለዓለም ማህበረሰብ እንድናስመሰክር አድርጎናልም “ ነው ያሉት።

በአብሮነት ቆመን ጠላቶቻችንን በማሳፈር ያገኘነው ድል ዘላቂ መሆን የሚችለው ብልፅግናን ለማረጋገጥ ከተጠቀምንበትና ከሰራንበት ብቻ ነው ሲሉ ተናግረዋል  ርዕሰ መስተዳድሩ።

ይህም ከህልውና ዘመቻ ትግላችን ተነጥሎ የማይታይ ሀገራዊ ግዴታችን በመሆኑ የክልሉ አመራሮች በከፍተኛ ኃላፊነትና ትጋት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የብልፅግና ጉዟችን ከጠራ የአመራር ተሳትፎ ውጭ አይሳካም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤  አመራሩ ወደ ታች በመውረድና ያሉትን ችግሮች በማጤን ለመፍትሄው አበክሮ  መስራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።

የክልሉ ነዋሪ ከሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦች ጋር በመሆን  የህልውና ጦርነቱን እንደመከተው ሁሉ በቀጣይም በመንግስት የታቀደው ዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልጽግና ውጥኖች እንዲሳኩ በላቀ ተነሳሽነት እንዲተጋም ጥሪ አቅርበዋል።

ዛሬ የተጀመረው የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የውይይት መድረክ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን  በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጥልቀት በመምከር ቀጣይ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል።