የጤና ተደራሽነትና ጥራትን ለማረጋገጥ ሁሉን አቀፍ የሰው ኃይል አቅም መገንባት ያስፈልጋል

93

አዲስ አበባ፣  ታህሳስ 21/2014(ኢዜአ) የጤና ተደራሽነትና ጥራትን ለማረጋገጥ ሁሉን አቀፍ የሰው ኃይል ግንባታ ላይ መስራቱን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስትሩ ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል የአዳዲስ የጤና ባለሞያዎች የቅጥር አማራጭ መርሃ ግብር ይፋ አድርጓል፡፡

የጤና ባለሞያው ከአገሪቷ የሕዝብ ብዛት አንጻር አነስተኛ ቁጥር ቢኖረውም ከዚህ በተቃራኒ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ቅጥር መፈጸም ባለመቻሉ በርካታ የጤና ባለሞያዎች ተመርቀው የስራ ዕድል ሳያገኙ ቆይተዋል።

የሚኒስትር ዴኤታ ጽህፈት ቤት ኃላፊዋ ወይዘሮ አዲስ ግርማ እንደገለጹት መርሃ ግብሩ የአዳዲስ ምሩቃን የጤና ባለሞያዎችን ስራ አጥነት በመፍታት ለኅብረተሰቡ ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ያለመ ነው።

ጤና ሚኒስቴር የስራ ዕድል አማራጩን በሶስት ዓመታት ለመተግበር ከአጋር አካላት ገንዘብ በመሰብሰብ ከመንግስት ጋር በወጪ መጋራት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የገንዘብ አቅሙን በማጠናከርም በመርሃ ግብሩ ማጠናቀቂያ የመንግስት ድርሻ እየቀነሰ መጥቶ ሚኒስቴሩ በራሱ አቅም የሰው ሀብት የመቅጠር አማራጭን ያሰፋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የጤና ሽፋን ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ካስቀመጠው ደረጃ በሰው ኃይልም ሆነ በጥራት ዝቅተኛ በመሆኑ ችግሩን በመንግስት አቅም ብቻ መፍታት ባለመቻሉ አጋር አካላትን ማሳተፍ ማስገደዱን ተናግረዋል፡፡

የሚኒስቴሩ የሰው ሀብት ልማት ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ደምሴ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገት ለማምጣት ፍትሃዊ የጤና ተደራሽነት አማራጭ የለውም ብለዋል።

ለዚህ ተግባራዊነትም የጤና ባለሞያዎችን ቁጥር ከሕዝብ ፍላጎት ጋር ለማስታረቅ የሰው ሀብት ልማት ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ጠቁመዋል።

አዲሱ መርሃ ግብርም የሰው ሀብት ልማትና የገንዘብ እጦትን ለመፍታት አዳዲስ አሰራሮችን መዘርጋት ያስችላል ነው ያሉት፡፡

ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው ሶስት ዓመታት ከ6 ሺህ በላይ አዳዲስ የጤና ምሩቃን የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

የክልል ጤና ቢሮዎች ኃላፊዎች በበኩላቸው መርሃ ግብሩ በጤና ዘርፍ የሚስተዋለውን የአገልግሎት አሰጣጥ እርካታ እንደሚያሳድገው ገልጸዋል፡፡

ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነት ትግበራው የክልሎችን የጤና ባለሞያዎች ቁጥር ማነስን በመለየት  ለፍትሃዊነቱ  ትኩረት እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡

መርሃ ግብሩ የጤና ዘርፉን መልከ ብዙ ችግሮች ለመፍታት ከመንግስት ብቻ ይጠበቅ የነበረውን ችግሮችን የመፍታት ስራ አጋር አካላትን ለማሳተፍ በሙከራ ደረጃ የጥናት መነሻ እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም