የአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች በህዝብ ይመረጣሉ

200

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21 ቀን 2014(ኢዜአ)የአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች በህዝብ እንደሚመረጡና ሹመታቸው በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንደሚጸድቅ የህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግስቱ በጋዜጣዊ መግለጫው እንዳሳወቁት የኮሚሽነሮች ጥቆማ መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ያካተተ ይሆናል።

ከተጠቆሙት 14 እጩዎች መካከል 11 ተመልምለው በአፈ ጉባኤው አቅራቢነት በምክር ቤቱ የሚሾሙበት አሰራር ተዘርግቷል፡፡

ኮሚሽነሮቹ በምክር ቤቱ ከተሰየሙበት እለት ጀምሮ ለ3 ዓመታት የሚቆይ የስራ ጊዜ የሚኖራቸው ሲሆን፤ እንደ አስፈላጊነቱ ቆይታቸው ሊራዘም እንደሚችልም ተገልጿል፡፡

በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ስለ ድርድር የሚገልጽ ምንም አይነት ይዘት አለመካተቱን ሰብሳቢዋ ጠቁመዋል፡፡

የአዋጁ ዋና አላማ እስካሁን መግባባት ላይ ያልተደረሰባቸውና የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተኑ የተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ያካተተ ውይይት በማድረግ ችግሮችን መፍታት እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

የሚቋቋመው ኮሚሽን ከምክክር መድረኮቹ የሚያገኘውን ምክረ ሀሳብ በመቀመር ተግባራዊ እንዲደረጉ እንደሚሰራ ጠቁመው፤ ምክር ቤቱን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ወስደው እንደሚያስፈጽሙና ለስኬታማነቱም ጠንካራ የክትትልና ቁጥጥር ስርዓት እንደሚዘረጋ ሰብሳቢዋ ተናግረዋል፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትላንት ባካሄደው 2ኛ ልዩ ስብሰባው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምጽ ስለማጽደቁ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ 

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️